
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብዙዎች ትርፍ አንጀት በሽታ እንደኾነ አድርገው ነው የሚመለከቱት። ለመኾኑ ትርፍ አንጀት በራሱ በሽታ ነው? በዛሬው የጤና አምዳችን ይህንን ርእሰ ጉዳይ እንዳስሳለን፦
አስማማው ተሾመ የትርፍ አንጀት ቀዶ ጥገና ያደረገ ወጣት ነው። ወጣት አስማማው ለአሚኮ እንዳለው በመጀመሪያ ሆዱን አካባቢ ከፍተኛ የኾነ ቁርጠት ይሰማው ነበር። የኾድ ሕመም ተደርጎም ስለተወሰደ ቤቱ ውስጥ ለቁርጠት ተብሎ ማር በቡና ተለውሶ፣ ስኳርም ይወስድበት የነበረ ቢኾንም ቁርጠቱ ግን አየጨመረ መጣ ይላል። እንቅስቃሴ ማድረግ ሁሉ አለመቻሉንም ያስታውሳል።
ሕመሙ ሲጠናም ወደ ሕክምና ተቋም ሄደ። በፍጥነት ምርመራ ሲደረግለት የትርፍ አንጀት ሕመም እንደኾነ እንደተነገረውም ይገልጻል። በፍጥነት መሠራት እንዳለበት እና ካልኾነ ግን ከፈነዳ ሕይዎቱን ሊያሳጣው እንደሚችል ሐኪሙ እንዳስረዱትም ተናግሯል።
ትርፍ አንጀቱንም በቀዶ ሕክምና ተወግዶ አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝም ወጣት አስማማው ያስረዳሉ። በተክለ ሃይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ምንተስኖት ፍጥረቱ ትርፍ አንጀት ሁሉም ሰው ላይ ያለ የአንጀት ክፍል መኾኑን ገልጸዋል።
ትርፍ አንጀት የሚገኘው በታችኛው የሆድ ክፍል በቀኝ በኩል ሲኾን የትልቁ አንጀት ተቀጥላ ነው። በአንጀት የበሽታ ተከላካይ ሥርዓት ውስጥም ሚና አለው ተብሎ ይታመናል ሲሉ ገልጸዋል። ዶክተር ምንተስኖት ፍጥረቱ እንደገለጹት ትርፍ አንጀት በመደበኛነት ወደ 9 ሴንቲ ሜትር የተጠጋ ርዝመት ያለው ሲኾን በአንዳንዶች ላይ ደግሞ እስከ 30 ሴንቲ ሜትር ሊረዝም እንደሚችልም ተናግረዋል።
ዶክተሩ ሰዎች በተለምዶ ስለትርፍ አንጀት ሕመም መንስዔዎች ያልተገባ እሳቤን ይዘው ይሄዳሉም ብለዋል። የትርፍ አንጀት ቁስለት ሲባል ደግሞ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሳቢያ የሚከሰትን የጤና ችግር ለማለት ያክል እንጂ ትርፍ አንጀት በራሱ ሕመም አይደለም ብለዋል ዶክተሩ።
የትርፍ አንጀት ቁስለት በሽታ ምክንያቶች ምን ይኾኑ?
👉 በአንዳንድ በሽታ ምክንያት በሆድ ውስጥ የሚፈጠር ማመርቀዝ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው የትርፍ አንጀት ቁስለት ህመም የሚከሰተው ሲሉ ዶክተር ምንተስኖት ገልጸዋል።
👉 ለትርፍ አንጀት ቁስለት ሕመም የሚያጋልጥ ቁራጭ ሠገራ በትርፍ አንጀት ውስጥ ተቀርቅሮ መቅረት እና በሠገራ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያወች የትርፍ አንጀትን በመመረዝ እንዲታመም ስለሚያደርጉ ነው ብለዋል።
የትርፍ አንጀት ቁስለት ሲከሰት ሕሙማን የሚያሳዩት ምልክቶች ምን ይኾኑ?👇
👉የማያቋርጥ እና እየጨመረ የሚሄድ የሆድ ሕመም፤ ሕመሙ በመጀመሪያ እምብርት አካባቢ ይጀምርና ወዲያውኑ ወደ ታችኛው ቀኝ የሆድ ክፍል ይዞራል፡፡
👉 መጠነኛ ትኩሳት፣ የሆድ ድርቀት፣ ተውከት ይኖራል፤ የምግብ ፍላጎትም ይቀንሳል፡፡
👉 እንዲሁም ደግሞ ሆድን በተቃራኒው ቦታ ሲጫኑት የህመም ስሜት መሰማትን ጨምሮ አንዳንድ ጊዜም እስከ ተቅማጥ ደረጃ ይደርሳል ብለዋል ዶክተሩ።
የትርፍ አንጀት ቁስለት በሽታን ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ ምንድን ነው?
እንደ ዶክተር መንተስኖት ፍጥረቱ ገለጻ 👇
👉የሕመምተኛውን ሆድ በስተግራ በኩል ከብሽሽቱ በላይ በዝግታ ጠንከር አድርጎ እስኪያመው ጫን ማለት እና ከዚያም እጅን በፍጥነት ማንሳት፡፡ እጅ በሚነሳበት ጊዜም እንደጦር የሚወጋ ሕመም ከተሰማው የትርፍ አንጀት ሕመም መኾኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በስተግራ በኩል ምንም ዓይነት ሕመም ካልተሰማው በስተቀኝ በኩል በድጋሚ መሞከር ይገባል፡፡
👉 በአብዛኛው በቀላል መንገድ ሕመሙ በሚያሳያቸው ምልክቶች ማወቅ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።
👉በተጨማሪም በሐኪም በሚደረጉ አካላዊ ምርመራዎች እንዲሁም በላቦራቶሪ በሚሠሩ ጠቅላላ የደም ሕዋሳት ቆጠራ ምርመራ እና የብግነት ጠቋሚ ምርመራዎች በመታገዝ ሊደረስበት ይችላል።
👉 ምስል ከሳች የኾኑትን የሆድ አልትራሳውንድ እና ሲቲ ስካን መሳሪያዎችን በማየትም መለየት ይቻላል ብለዋል።
እንደ ዶክተሩ ገለጻ የትርፍ አንጀት ቁስለት በቶሎ ካልታከመ የትርፍ አንጀት ወደ መፈንዳት ያመራል ነው ያሉት። በከፊል አለያም በሙሉ የአንጀት መዘጋትን በማስከተል የሆድ መነፋትን ጨምሮ አየር እና ሰገራ ማሳለፍን ሊዘጋ እንደሚችልም አብራርተዋል።
አጠቃላይ የሆድ እቃ ቁስለት፣ መግል መቋጠር እና የደም ውስጥ የባክቴሪያ ስርጭት ኢንፌክሽን በማድረስ ሕይዎትን እስከ መቅጠፍ ያደርሳል ሲሉ ዶክተር ምንተስኖት ተናግረዋል።
ችግሩ በሁሉም ሰው ላይ ሊከሰት እንደሚችል የገለጹት ዶክተሩ በተለይ በዕድሜ የገፉት እና በሕጻናት ላይ የመታየት ዕድሉ ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
በመኾኑም መሰል የሕመም ስሜቶች ሲያጋጥሙ የትርፍ አንጀት ቁስለት ሊኾን ስለሚችል በአስቸኳይ የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊገኝ ወደ ሚችልበት ሆስፒታል መሄድ አስፈላጊ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
