ባሕር ዳር: ሕዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች አሥተዳደር ዐቢይ ጉባኤ መደበኛ ጉባኤውን ሕዳር 25/2018 ዓ.ም ያካሄደ ሲሆን፣ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ መክሮ ውሳኔ መስጠቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለአሚኮ የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡
መዚህም መሠረት

169 የወረዳ ፍርድ ቤት ረዳት ዳኞች እና 5 የአዲስ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች በድምሩ የ174 ዳኞች ሹመት ለክልሉ ምክር ቤት እንዲቀርብ ወስኗል፡፡

4 የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሸሪዓ ዳኞች እና 25 የወረዳ ፍርድ ቤት ሸሪዓ ዳኞች ሹመት ሰጥቷል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ደሴ እና ጎንደር ምድብ ችሎት አስተባባሪዎች ከኃላፊነት እንዲነሱ ወስኗል።

የአንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የተጠረጠሩበትን ሃሰተኛ ሰነድ መፍጠር እና የአንድ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ የተጠረጠሩበትን የአካል ጉዳት ማድረስ እና ዛቻ ወንጀል መነሻ በማድረግ ከተወያየ በኋላ ያለመከሰስ ከለላቸዉን አንስቷል።

የዲሲፒሊን ጉዳዮችን መርምሮ ሁለት የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች ከኃላፊነት እንዲነሱና ውሳኔው በክልሉ ምክር ቤት እንዲጸድቅ የውሳኔ ሀሳብ ሰጥቷል፡፡ እንዲሁም በሌሎች የዲሲፕሊን ጉዳዮች ላይ መክሮ የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ሌሎች የቅሬታ ይግባኞችን መርምሮ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፣ ተጨማሪ ማጣራት የሚያስፈልጋቸው የዲሲፒሊን ጉዳዮች በቀጣይ ጉባኤ ተጣርተው እንዲቀርቡ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በተጨማሪም የቀረበለትን የዝውውር መረጃ መርምሮ ለኅብረተሰቡ የተሻለ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ሲባል በጥናት ላይ የተመሰረተ የመመሪያ ማሻሻያ ተደርጎ አስኪተገበር ድረስ መደበኛ ዝውውር ለጊዜዉ ታግዶ እንዲቆይ እና በሚወጣው መመሪያ መሰረት ውድድር ተደርጎ እንዲተገበር ሆኖም እንደአስፈላጊነቱ በልዩ ዝውውር የሚቀርቡ የዝውውር ጥያቄዎች እንዲስተናገዱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ጉባኤው የተያዙ አጀንዳዎችን ከመመርመሩ በፊት የጠቅላይ ፍርድ ቤት የትኩረት አቅጣጫዎች እና እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች በክቡር ፕሬዚዳንት አለምአንተ አግደው ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡