
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ኅብረት በአማራ ክልል መንግሥት እና በአፋሕድ መካከል የተደረገውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት አወድሷል፡፡
የሰላም ስምምነቱ በአካባቢው ለዓመታት የዘለቀውን ግጭት አስቁሞ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ርምጃ ነውሞ ብሎታል፡፡
በአዲስ አበባ በተካሄደው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ሰልማ ማሊካ አዳዲ እና የኢጋድ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ መሐመድ አብዲ ዋሬ ተገኝተዋል።
ኅብረቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መልእክት የኅብረቱ ምክትል ሊቀመንበር ሰልማ ማሊካ አዳዲ የክልሉ መንግሥት እና ታጣቂዎቹ ለውይይት እና ለሰላማዊ መፍትሄ ያደረጉትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ይህ ስምምነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለመላው የአፍሪካ አሕጉር ወሳኝ ምዕራፍ መኾኑንም አፅንኦት ሰጥተው አንስተዋል።
ምክትል ሊቀመንበር ሰልማ ማሊካ አዳዲ “እያንዳንዱ የሰላም ስምምነት የጥይት ድምፅ የማይሰማባት አሕጉር የመገንባት ግባችን ላይ ለመድረስ ያግዘናል” ብለዋል።
“በአፍሪካ ኅብረት ስም የዘላቂ ሰላም ስምምነት ተፈራራሚዎቹ ከዚህ አስፈላጊ ምዕራፍ ላይ በመድረሳቸው እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ ነው ያሉት።
የሰላም ስምምነቱ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት ያለንን ቁርጠኛ አቋም ያንፀባርቃልም ብለዋል፡፡
ኅብረቱ ለስምምነቱ ተግባራዊነት እና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሰፊ የሰላም መሻት ለመደገፍ ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
