
ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ “ትውልድን በሥነ ምግባር ተቋምን በአሠራር መገንባት” በሚል መሪ መልዕክት የጸረ ሙስና ቀንን አክብሯል።
ቀኑን ምክንያት በማድረግ ሙስናን እና ብልሹ አሠራሮችን በመታገል ዙሪያ መክሯል። በምክክሩ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲኾን የውይይቱ ተሳታፊዎች ሀሳብ እና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ብልሹ አሠራሮችን በቁርጠኝነት መታገል፣ ፖሊሳዊ ሥነ ምግባርን መከተል፣ የፖሊስ ሠራዊቱ አንድ አይነት አመለካከት ሊይዝ እንደሚገባ፣ ሁሌም የሕዝብ አገልጋይነትን አክብሮ መሥራት፣ በየደረጃው በተቋሙ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ እና ለሕዝብ ታማኝ ኾኖ ማገልገል እንደሚገባ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) ሙስና እና ብልሹ አሠራር ፍትሐዊነትን ስለሚያዛባ በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።
ችግሩን ለመፍታት ተቋማዊ አሠራሮችን ማጠናከር፤ የቁጥጥር እና የክትትል ሥርዓትን ማዘመን እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ሌብነትን ለመከላከል መንግሥት ብቻውን የሚወጣው ሳይኾን ሁሉም ማኅበረሰብ የራሱን ሚና መወጣት ይገባል ነው ያሉት።
የፖሊስ ተቋሙ ሙስናን፣ ሌብነትን እና አድሏዊ አሠራርን በሚፈጽሙት ላይ ተከታትሎ ወደ ሕግ በማቅረብ የተጣለበትን ኅላፊነት የሚወጣ ተቋም ነው ብለዋል።
የፖሊስ ሠራዊት የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ፣ በታማኝነት ያለ አድሎ አገልግሎት ለመስጠት፣ አድሏዊ አሠራሮችን ለማስወገድ ቃለ መሀላ ፈጽሞ ወደ ሥራ የገባ ኃይል ነው ብለዋል። ራሱን ከየትኛውም የሙስና እና ብልሹ አሠራር በማጽዳት በግንባር ቀደምትነት ሊታገል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሥነ ምግባር የተመሠገነ፣ እጁ የነጻ፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን የሚጸየፍ እና የሚታገል የፖሊስ ተቋም እየተገነባ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ሌብነትን እና ብልሹ አሠራርን ለማስተካከል በተቋሙ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በየደረጃው የሚገኝ የፖሊስ መሪ እና አባላት በንጽሕና ለሕዝቡ አገልግሎት የሚሰጥ መኾን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
