ዲጂታል ሉዓላዊነት ምንድን ነው?

11

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የምጣኔ ሃብት ፎረም በድረ ገጹ ያወጣው ጽሑፍ የዲጂታል፣ የሳይበር፣ የቴክኖሎጂ እና የዳታ ሉዓላዊነት ዲጂታል እጣ ፈንታችንን ለመቆጣጠር የምንችልበት መንገድ እንደኾነ ይገልጻል።

ይህም በምንፈጥራቸው እና በምንጠቀማቸው መረጃዎች፣ መተግበሪያዎች እና የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች ላይ የሚኖረንን የመቆጣጠር አቅም የሚገልጽ ነው። ፎረሙ ዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማስረዳት የአፍሪካ እና የአውሮፓ ግንኙነት ማዕከልን ዋቢ በማድረግ በሦስት ደረጃ አስቀምጧል። እነዚህ ደረጃዎች በቁስ የሚገለጹ ቴክኖሎጂዎች፣ በኮድ ደረጃ የሚገለጹ መተግበሪያዎች እና መረጃዎች ናቸው።

ማይክሮሶፍት ደግሞ ዲጂታል ሉዓላዊነትን ሲገልጽ ተቋማት ወይንም መንግሥት ዲጂታል ሃብቱን ደኅንነቱ በተጠበቀ እና ነጻ በኾነ መንገድ መጠቀም የማያስችል ነው ይለናል።

ደኅንነቱ በተጠበቀ እና ነጻ በኾነ መንገድ መረጃን እና ቴክኖሎጂን መጠቀም በዲጀታል ሥርዓት ከተሳሰረው ዓለም መነጠል ሳይኾን የራስን ምርጫ እና ውሳኔ ያለ ማንም ተጽዕኖ የመፈጸም አቅም መኾኑንም ማይክሮሶፍት ገልጿል።

ዲጂታል ሉዓላዊነትን የበለጠ ለመረዳት ቁልፍ እንደኾኑ ማይክሮሶፍት የገለጻቸው ሦስት ምሰሶዎች የዳታ ቁጥጥር፣ የትግበራ ቁጥጥር እና የቴክኖሎጂ ነጻነት ናቸው። የዳታ ቁጥጥር መረጃውን ማግኘት የሚችለው ማን ነው? የት ነው የሚቀመጠው እና እንዴት ነው የሚቀናበረው የሚለውን የሚወስን ነው።

የትግበራ ቁጥጥር የሚባለው ደግሞ ተቋማት የአተገባበር ግልጽነት እንዲኖራቸው እና በዲጂታል ሃብት አጠቃቀም ላይ የመጠቀም ሥልጣን የሚሰጣቸው ነው። የቴክኖሎጂ ነጻነት የምንለው ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በራስ ፍላጎት የዲጂታል መሠረተ ልማት እና መተግበሪያዎችን የመጠቀም ነጻነት ነው።

ዲጂታል ሉዓላዊነት ሲከበር ለአንድ ሀገር ሊያበረክት የሚችለውን ጠቀሜታ ለማግኘት ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ አብዛኞቹ የሚሰማሙ መኾኑን በተለይ ደግሞ ብሔራዊ የደኅንነት ሥጋት ሊፈጥሩ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ወሳኝ ጉዳይ ነው ሲል ዊፎረም ድረ ገጽ አስነብቧል።

ቢኾንም ቴክኖሎጂዎች እና መረጃዎች የሚተዳደሩበት መንገድ ከሀገር ሀገር የሚለያይ መኾኑንም ጠቁሟል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ በ2030 ስትራቴጂ ውስጥ ከተካተቱ ቀልፍ ጉዳዮች አንዱ ዲጂታል ሉዓላዊነት መኾኑም ይታወቃል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመሬት ካሳ አከፋፈል ሕጉ ምንን ያስቀምጣል?
Next articleቀይ ባሕር እና ጂኦ ፖለቲካዊ አንድምታው