ባለኮከብ ሆቴሎችን ለመገንባት ቦታ የወሰዱ ባለሃብቶች በፍጥነት አጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሠጡ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።

15
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ለልዩ ልዩ የሆቴል እና ቱሪዝም አገልግሎቶች ቦታ ከወሰዱ ባለሃብቶች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎችም የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች እየተሳተፉ ነው።
ባለኮከብ ሆቴሎችን ለመገንባት ቦታ ከተረከቡ በኋላ ሕንጻ ቢገነቡም አገልግሎት ግን መስጠት ያልጀመሩ፣ ሕንጻ ግንባታ ጀምረው ያላጠናቀቁ እና ቦታውን አጥረው ያስቀመጡ በአጠቃላይ 43 ባለሃብቶች በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባለሃብቶች ለማልማት የወሰዱትን መሬት በፍጥነት አልምተው የታለመውን አገልግሎት እንዲሰጡ ልዩ ድጋፍ እና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
መንግሥት አሥፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል፤ ሰበብ እያበዙ ውድ የኾነውን መሬት አጥረው የሚያስቀምጡ ባለሃብቶች ሲገጥሙ ደግሞ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል።
“ለኢንቨስትመንት ትልቁ ጸጋው ሕግ ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ባለሃብቶች ሕግን ተከትለው የወሰዱትን መሬት ማልማት አለባቸው፤ ካልኾነ ግን የዘርፉ መሪዎች መከታተል እና በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ሕግ ማስከበር አለባቸው ነው ያሉት።
በተለያዩ ከተሞች የሆቴል ግንባታ ወስደው በፍጥነት የሚያለሙ ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ምስጋናም አቅርበዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
ሰበብ እየደረደሩ ለበርካታ ዓመታት የሚዘገዩ ባለሃብቶች መኖራቸውንም አንስተዋል። በእንዲህ አይነት ባለሃብቶች ላይ የማያዳግም እና ቁርጠኛ እርምጃ እንደሚወሰድም በአጽንኦት ገልጸዋል።
ክልሉ ለሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ በተመቹ ትላልቅ ከተሞች የታደለ መኾኑንም ጠቅሰዋል። መሪዎች እና ባለሃብቶች በመወያየት ይህንን ጸጋ መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዋነኛ የቱሪዝም ጸጋ ነው፤ በቀጣይ የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችንም ለማስተናገድ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል። በስታዲየሙ ከፍለው ለመጫወት ከወዲሁ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሀገራት መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
ባለሃብቶች ተጨማሪ ዘመናዊ እና ባለኮከብ ሆቴሎችን ፈጥነው በመገንባት የራሳቸውን ኢኮኖሚ ማሳደግ እና ለከተማዋም ገጽታ ባለውለታ መኾን አለባቸው ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ ዓለም አቀፍ እንግዶቿን ተቀብላ በከፍታ ለማስተናገድ የሚያስችሉ ተጨማሪ ዘመናዊ ሆቴሎች ያስፈልጓታል ብለዋል። ለዚህም የሚኾን ቦታ ለአልሚ ባለሃብቶች እየቀረበ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
በከተማዋ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ቦታ ወስደው እስካሁን አገልግሎት ያልጀመሩ ባለሃብቶችን ከተማ አሥተዳደሩ እየደገፈ መቆየቱንም ተናግረዋል። የወሰዱትን መሬት በኀላፊነት ይዘው በማልማት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሃብቶችንም አመስግነዋል።
በወሰዱት መሬት ላይ ግንባታቸውን አጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት ሲገባቸው ሰበብ እየፈጠሩ ያለልማት ከመቆየት አዝማሚያ ያልወጡ ባለሃብቶችም አሉ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።
እነዚህ ባለሃብቶች ለራሳቸው ተጠቃሚነት እና ለከተማዋም ልማት በማሰብ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
አልሚ ባለሃብቶች ለሚያነሷቸው ትክክለኛ ጥያቄዎች ከተማ አሥተዳደሩ ከቢሮክራሲ በጸዳ መልኩ እና በፍጥነት ለመፍታት ዝግጁ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ለሰበብ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን እና የከተማዋን ልማት የሚጎዱ የባለሃብቶችን ቸልተኝነትም በመከታተል ለማስተካከል እንሠራለን ብለዋል።
የቁርጠኛ ባለሃብቶችን የልማት ማስፋፊያ ጥያቄዎች በሙሉ ከተማ አሥተዳደሩ ተቀብሎ መፍትሔ ስለመስጠቱም ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) የሆቴል አልሚዎች ከዘርፉ የመንግሥት መሪዎች ጋር በቅርበት በመሥራት ለከተሞች ውበት የሚመጥኑ ሥራዎችን ማከናወን አለባቸው ብለዋል።
በመንግሥት በኩል የፕሮጀክት አፈጻጸም ባሕል እየተገነባ ነው፤ 24 ሰዓት የማያቋርጥ አሠራርም ተገንብቷል፤ ባለሃብቶችም ይህንኑ ባሕል ወስደው የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች በፍጥነት ማጠናቀቅ አለባቸው ብለዋል።
ቱሪዝም ለከተሞች መነቃቃት ዋነኛ ግብዓት መኾኑን ጠቅሰው በሆቴል ግንባታ ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶች በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት። በተለይም ባሕር ዳር ከተማ ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ የሚካሄድባት ከተማ ስለኾነች በከተማዋ የተጀመሩ የባለኮከብ ሆቴል ግንባታዎች በፍጥነት ተጠናቅቀው አገልግሎት መጀመር አለባቸው ብለዋል።
ከሰበብ መውጣት ችግሮችን በጋራ መፍታት እና ጅምር ሥራዎችን ማጠናቀቅ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
አልሚ ባለሃብቶችም ውይይቱ ለሥራቸው መልካም አጋጣሚ መኾኑን ተናግረዋል። የፋይናንስ ችግር፣ የግንባታ ወቅት የዲዛይን ማሻሻያ፣ የማስፋፊያ ጉዳይ፣ የድንበር ውዝግቦች እና የቦታ ከሦስተኛ ወገን ነጻ አለመኾን ዋና ዋና የሥራ እንቅፋቶች እንደኾኑባቸው ጠቅሰዋል። ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመነጋገር ችግሮቹን እየቀረፉ በፍጥነት ወደ ሥራ እንደሚገቡም በመድረኩ ላይ አረጋግጠዋል።
በቀጣዩ ወር እንደገና በመገናኘት የባለሃብቶቹ አዲስ የሥራ እንቅስቃሴ ከርእሠ መሥተዳድሩ ጋር በመኾን እንደሚገመገምም ቀጠሮ ተይዟል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መመሪያዎች በየወቅቱ ቢወጡም ተግባራዊ ማድረግ ላይ ግን ክፍተት አለ።
Next articleስለ ሰላም በአንድነት እንነሳ።