
ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከደብረ ማርቆስ ከተማ
አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ከተማዋ በሀገር መከለካያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ ኃይል መስዋዕትነት፣ በከተማዋ ነዋሪዎች ሰላም ወዳድነት ወደ አንጻራዊ ሰላም ተሸጋግራለች ብለዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከሕዝብ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውንም ተናግረዋል።
በከተማዋ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። የተገኘው ሰላም ልማትን ለማረጋገጥ መደላድል የሚፈጥር እንጂ በቂ አለመኾኑንም ተናግረዋል። አሁንም ዘላቂ ሰላም አለመረጋገጡን እና ወደተሟላ ልማት አለመገባቱን ገልጸዋል። ባለሃብቶችም በሚፈለገው ልክ ወደ ሥራ አለመግባታቸውን አመላክተዋል።
ሰላምን በማረጋገጥ ወደ ተሟላ ሰላም መሸጋገር እንደሚገባ ነው የገለጹት። ከግጭት እና ከድህነት አዙሪት መውጣት የምንችለው በመግባባት እና በተባበረ ክንድ ነው ብለዋል። በመሳሳብ እና በመጓተት፣ በመለያየት እና በመጠፋፋት የሚመጣ ልማት እና የሚረጋገጥ ብልጽግና አለመኖሩንም ተናግረዋል።
ለችግሮቻችን መፍትሔ የሚኾኑ መካሪ አባቶች ሳናጣ በግጭት ውስጥ መቆየት ያሳዝናል ነው ያሉት። ጊዜው በፍጥነት የመልማት፣ የተወዳዳሪነት፣ በቴክኖሎጂ የመመዘን፣ አልቆ የመሥራት እና አልቆ የማሰብ እንጂ በኋላ ቀር የፖለቲካ ባሕል መጓዝ አይደለም ብለዋል።
ችግሮችን በውይይት በመፍታት ወደ ተሟላ ሰላም እና ልማት መግባት ይገባናል፤ ለዚህ ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር እና በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከበፊቱ የተሻለ አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል ብለዋል። ነገር ግን አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላምን መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
አሁንም የተሳለጠ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የለም፣ ተማሪዎች በተሟላ ሁኔታ ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም ብለዋል።
አሁንም የመንቀሳቀስ ነጻነት፣ ሠርቶ የመብላት ነጻነት እንደሌለ ተናግረዋል። በታሪካችን እና በባሕላችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰዎች እየታገቱ ገንዘብ ይጠየቅባቸዋል ነው ያሉት።
በሃይማኖት አባቶች እና በሕጻናት ላይ ሳይቀር ግፍ እንደሚፈጸምም ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መወያየት እና ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል። ለሰላም መረጋገጥ መንግሥት ከሚጠበቅበት ሚና ሕዝብም የራሱን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው ገልጸዋል።
የደብረ ማርቆስ እና የምሥራቅ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች በልማት ተጠቃሚ ለመኾን ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሌሎች አካባቢዎች እየለሙ ነው፤ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎችን ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ በልማት ተጠቃሚ መኾን አለባቸው ብለዋል።
በውይይት እና በመግባባት ዘላቂ ሰላምን ማስፈን፣ ለልማት የተመቸች ከተማ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት። “የሚመክሩ፣ አቅጣጫ የሚያመላክቱ እና የራሳቸውን ሚና የሚወጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንፈልጋለን” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
