“ዓለም ችግሩን የፈታው በውይይት ነው፣ እኛም ችግሮቻችን በንግግር እንፍታ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

23
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከአዋበል ወረዳ እና ሉማሜ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደን ጨምሮ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መንግሥት የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ቆጥሮ በመለየት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በግጭት የሚፈቱ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች አለመኖራቸውንም ገልጸዋል።
መንግሥት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። እስካሁን ድረስ የተዛነፉ ትርክቶችን በማስተካከል ገዢ ትርክት ለመገንባት እየተሠራ ነው ብለዋል።
“ዓለም ችግሩን የፈታው በውይይት ነው፣ በጦርነት አይደለም፤ እኛም ችግሮቻችን በንግግር መፍታት አለብን” ነው ያሉት። መንግሥት ችግሮች በውይይት መፈታት አለባቸው ብሎ እንደሚያምንም ተናግረዋል።
ወደ ጫካ የወጡ ኃይሎች ለሕዝብ እንሠራለን በሚል የማደናገሪያ ሃሳብ ተነስተው ከአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየሠሩ ሕዝብን ለከፋ ችግር መዳረጋቸውንም ገልጸዋል። ይህም ዓላማ እና ግቡ ከጠላት ጋር ተባብሮ ሀገር ማፈረስ ነው ብለዋል።
በሚያነሱት የማደናገሪያ ሃሳብ ሕዝብ መደናገር እንደማይገባውም አስገንዝበዋል። መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አቅርቧል፤ ብዙዎችም ተቀብለውታል፤ እስካሁን ድረስ ጥሪውን ያልተቀበሉም አሉ ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
ሕዝባችን ሰላም እንዲያገኝ አሁንም ለሰላም ዝግጁ ነን፤ ለሰላም ተስፋ አንቆርጥም፤ የመጨረሻው መቋጫም ሰላም እንደኾነ እናምናለን ብለዋል። ከውጭ ኃይሎች ተልዕኮ እየተቀበሉ ሀገርን በጦርነት ለማተራመስ እየሠሩ ያሉ አካላት መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ከግጭት እና ከድህነት አዙሪት ለመውጣት ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። ትምህርት ከየትኛውም የፖለቲካ እሳቤ ገለልተኛ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ነገር ግን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ ተደርጓል ብለዋል።
ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ በማድረግ የሕዝብ ጥያቄ አይመለስም፤ ይህን አካሄድ በቃ ልትሉት ይገባል ነው ያሉት።
የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚሠራም ተናግረዋል። የመልካም አሥተዳደር እና የአግልግሎት አሰጣጥ ችግሮችም ይፈታሉ ነው ያሉት። መሪዎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡም አሳስበዋል።
ከተናጠላዊ ሁኔታ በመውጣት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር እና የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትኾን ከግጭት አዙሪት መውጣት እና ለሀገር ልማት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሰላማቸውን መጠበቅ፣ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በአንድነት መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleትርፍ ያለው ከሰላም ብቻ ነው።
Next article“አሚኮ ለሀገር እድገት የሚበጅ የመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ጠንካራ ተቋም ነው” ሚኒስትር ዴኤታ ስለሽ ግርማ