በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሪፎርም ወደ ተግባር መቀየር ያስፈልጋል።

12
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን “ኅብረት ሥራ ስለኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት ለኅብረት ሥራ አመቻች ባለሙያዎች በባሕር ዳር ከተማ ሥልጠና እየሰጠ ነው።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብዱ ሙመድ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ እድገት ለማምጣት ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሀገር እድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል። ውጤታማ ኾነው መንግሥት የጀመራቸውን የልማት ሥራዎችን እንዲደግፉ ለማስቻል ሪፎርም መሠራቱን ተናግረዋል።
በሚፈለገው ልክ ለውጥ ማምጣት እንቅፋት የኾኑትን ጉዳዮች በጥናት መለየቱንም አብራርተዋል። የፖሊሲ፣ የአሠራር፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ የአደረጃጀት፣ የገበያ መረጃ ተደራሽነት፣ የገንዘብ አቅርቦት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ሌሎች ችግሮች በጥናት መለየታቸውን አመላክተዋል።
የሥልጠናው ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የኅብረት ሥራ ሪፎርም ወደ ተግባር ለመቀየር መኾኑንም አንስተዋል። ሠልጣኞች ሥልጠናውን በሚገባ ወስደው በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ያሉትን ባለሙያዎች በመደገፍ ሪፎርሙን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት አማረ በክልሉ እስከ ቀበሌ ድረስ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አደራጆች መኖራቸውን አንስተዋል። ለረጅም ጊዜ በተደራጀ መንገድ ሳይሰጥ መቆየቱን አንስተዋል።
በኮሚሽኑ የተሠራውን ሪፎርም ተከትሎ ለክልሉ ባለሙያዎች ሥልጠና መሥጠቱ የባለሙያዎችን አቅም እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።
በየደረጃው ያለውን ባለሙያ በአሠራሮች ዙሪያ ግልጽ ግንዛቤ እንዲይዝ በማድረግ ማኅበራትን እንዲደግፉ የሚደረግበት ነው ብለዋል። ሥልጠናው ልምድ የሚለዋወጡበት ተደርጎ የተዘጋጀ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
እንደ ክልል በተዘጋጀው የአምስት ዓመታት እቅድ እና የ25 ዓመታት የልማት እቅድም በዘርፉ የተጣለውን ግብ ለማሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ሰፊ ግንዛቤ የሚፈጠርበት ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ መሰጠት በጀመረው ሥልጠና ከምዕራብ አማራ ቀጣና የመጡ 761 የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። በቀጣይም በምሥራቅ አማራ ቀጣና ለሚገኙ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ተመላክቷል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰባት ክልሎች ለ3 ሺህ 280 የኅብረት ሥራ ማኅበራት የልማት አመቻች ሥልጠናው እየተሰጠ እንደሚገኝም ተገልጿል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኤችአይቪ ኤድስን በመከላከል ጤናማ ትውልድ መገባት ያስፈልጋል።
Next articleአምባሳደር በትረ መንግሥቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሚኒስትር ዴኤታ ኾነው ተሾሙ።