“እየተመዘገበ ላለው የግብርና እድገት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ትልቅ ድርሻ ይወስዳሉ” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)

9
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፌደራል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ለአመቻች ባለሙያዎች ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ልማት ሥልጠና በባሕር ዳር እየሠጠ ነው።
በሥልጠናው ማሥጀመሪያ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሠ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሀገሪቱ ለጀመረችው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ዋነኛ አሳላጭ መሳሪያ እንዲኾኑ ለማድረግ አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የፋይናንስ አቅማቸው እየዳበረ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ እና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን እንዲደግፉ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ ማኅበራት ዋነኛ የእድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ኾነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ እየተመዘገበ ላለው የግብርና እድገት የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ ነው ያሉት። በማዳበሪያ፣ በምርጥ ዘር ሥርጭት፣ ገበያ በማረጋጋት እንዲሁም ለአርሶ አደሮች በቴክኖሎጂ አቅርቦት አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
ክልሉ ያዘጋጀውን የአምስት ዓመታት ስትራቴጅክ እቅድ ለማሳካትም የኅብረት ሥራ ኮሚሽን ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል። የኅብረት ሥራ ኮሚሽንም የዘርፉን የሰው ኀይል በማሠልጠን በኩል ለክልሉ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ሠልጣኞች “በክልሉ እየተቀጣጠለ ያለውን የኢኮኖሚ አብዮት የምታሳለጡ በመኾናችሁ ክልሉ ለሚፈልገው እድገት እና ልማት የበኩላችሁን እንድትወጡ እና አሻራችሁን እንድታስቀምጡ አደራ እላለሁ” ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሀገር በቀል እውቀትን የሚያበረታታ የፈጠራ ሥራ እየተሠራ ነው።
Next article“ጉዳዩን የተገነዘበ እና የተደራጀ ሕዝብ ሲኖር ሰላም አስተማማኝ ይኾናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ