
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአንጎላ ሉዋንዳ እየተካሄደ ባለው 7ኛው የአፍሪካ እና አውሮፓ ኅብረት የሩብ ምዕተ ዓመት የትብብር ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የዓለም የፋይናንስ እና የፀጥታ ተቋማት ኢ-ፍትሃዊነት ጊዜው ያበቃ በመኾኑ የአፍሪካ ድምፅ ጉልህ ኾኖ እንዲሰማ የሚያስችል ማሻሻያ እንዲሠራ ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ የ2030 የትብብር ግቦችን ለማሳካት ቅድሚያ የሚሰጠው የሰላም እና ደህንነት ጉዳይ ሲኾን ኢትዮጵያም ለዚህ ዘርፍ ትልቅ ዋጋ ከፍላለች ብለዋል።
በሱዳን ያለውን አስከፊ ጦርነት መቋጫ ሊበጅለት ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ ከሱዳናውያን በሚመነጭ እና በአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ እገዛ ሱዳን ወደ ቀደመ ሰላሟ መመለስ ይኖርባታል ሲሉም አሳሰበዋል።
በውጫዊ ጫናዎች ምክንያት በአፍሪካ እየጨመረ የመጣውን የመንግሥታት አለመረጋጋት፣ የተራዘመ ግጭት እና ሕገ-መንግሥታዊ ያልኾነ የመንግሥት ግልበጣን በአስቸኳይ ማስወገድ እንደሚገባ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ለዚህ ዝግጁ መኾኗን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ኢትዮጵያ የብዝኅ ትብብርን አጠናክራ እንደምትቀጥል እና ለሰላም እና ልማት መሳካት ቁልፉ በጋራ መሥራት መኾኑን አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ የመጪው ዘመን ተስፋዎች ወጣቶች ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ የአውሮፓ ኅብረት በኢንቨስትመንት ፓኬጁ በኩል በታዳሽ ኃይል፣ በዲጂታል ሽግግር እና በፈጠራ ሥራዎች ላይ የሚደረገውን ድጋፍ እንዲጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በባብ-ኤል-መንደብ ላይ ያንዣበበው ስጋት በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
