
አዲስ አበባ: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስምምነቱ ዓለም አቀፍ አሠራሮችን በመከተል በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ መኾኑ ተመላክቷል።
ኢትስዊች እና ጀነሲስ አናሊቲክስ ይህን ስምምነት የተፈራረሙት ፈጠራ የታከለበት፣ አስተማማኝ እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱን የሚያጠናክሩ መፍትሄዎችን ለፋይናንስ ተቋማት ለማቅረብ ነው ተብሏል።
ሥምምነቱ ሸማቾችን በተቀላጠፈ የዲጂታል ሥርዓት ተጠቃሚ የሚኾኑበትን አሠራር የበለጠ ለማጠናከር ካላቸው የጋራ ቁርጠኝት በመነሳት መኾኑንም በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተነግሯል፡፡
በዚህ አጋርነት መሠረት ኢትስዊች እና ጀነሲስ አናሊቲክስ የተለያዩ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት አቅሞችን ለማሳደግ እና ለመተግበርም አብረው ይሠራሉ ተብሏል።
ዲጂታል የገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ከፈጣን ኔትዎርክ ጋር እንዲተሳሰር እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቢዝነሶችም ዓለም አቀፍ ክፍያዎችን እንዲቀበሉ እና ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥም ለማድረግ እድሎችን ለማስፋት እንደሚያስችል ተነግሯል።
በሥምምነት መርሐ ግብሩ ላይ የኢትስዊች እና የጀነሲስ አናሊቲክስ ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የቦርድ አባላት እና ሠራተኞች ታድመዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
