የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ኾነን ልናከብረው ይገባል።

12
አዲስ አበባ: ኅዳር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የክልሉን አሁናዊ ሁኔታ እና የተሠሩ ተግባራትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የቢሮው ኀላፊ ዘሪሁን እሸቱ ዘንድሮ በክልሉ የሚከበረው 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ለክልሉ ዕድል እና ጸጋን ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል። በተለይም በክልሉ ተጀምረው የነበሩ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አስችሏል ብለዋል።
ክልሉ ዝግጅቱን አጠናቅቆ እንግዶችን በመጠባበቅ ላይ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው የኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የኾነውን በዓል በወንድማማችነት መንፈስ እና በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ኾኖ ማክበር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በክልሉ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን በተመለከተም ክልሉ ከሀገር አቀፍ ኢኒሼቲቮች በሻገር በራሱ አቅም በማስጀመር የክልሉን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የአርሶ አደሮችን ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ገበያ ተኮር ግብርናን በማስተሳሰርም ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት ኀላፊው በመግለጫቸው።
ክልሉ ሲመሠረት የተለያዩ ስጋቶች እንደነበሩበት በመግለጽም እነሱን ለመቀልበስ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ የመሥራት፣ ክልሉ ያሉትን ጸጋዎች በአግባቡ የመጠቀም፣ ሕዝቡን ከተረጂነት ወደ አምራችነት የማሸጋገር እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ መሠራቱንም ጠቁመዋል።
በቱሪዝም፣ በከተማ እና በገጠር ኮሪደር ልማት፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ ንቅናቄ፣ በመስኖ ልማት፣ በገቢ አሰባሰብ እና በመሰል ሥራዎች ክልሉን ለማልማት እና ሕዝቡንም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በክልሉ በሚሠሩ የልማት ሥራዎች ላይ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ በየግዜው እያደገ መምጣቱንም ዘሪሁን እሸቱ ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ579 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ምርቶች የተሸፈነ ሲኾን ከዚህም ከ37 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ በመግለጫው ላይ ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ቤተልሔም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአቡዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ ካሌድ ቢን መሐሙድ ቢን ዛይድ አልናህያን ጋር ተወያዩ።
Next article“ስፓኒሽ ፍሉ”