
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ በማፋጠን ከተሞቻችን ከፍተኛ ሚና ናቸው ብለዋል።
በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ሲካሄድ የቆየውና ዛሬ በድምቀት ያጠናቀቅነው 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የከተሞቻችንን የዕደገት ጉዞና ተስፋ በግልፅ ያሳየ ነው።
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ የሥልጣኔ መሠረት የሆኑትን ከተሞቻችንን የብልጽግና ማሳያዎችና ማዕከላት አድርጎ ይመለከታቸዋል ነው ያሉት።
በብልጽግና ማዕከልነታቸው የብዝኃ ዘርፍ ኢንዱስትሪ ማበቢያ ቦታዎች ሲሆኑ፣ በብልጽግና ማሳያነታቸው ደግሞ የሁለይተናዊ የዕድገት ጉዟችንና የክትመት ማዘመን ሥራችን ወደ ገጠር እንዲሰፋ መሠረት እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በመዲናችን አዲስ አበባ የጀመርነው ከተሞችን ለብልጽግና ጉዞ የማመቻቸት እንቅስቃሴ ዛሬ ወደ አነስተኛ የገጠር ከተሞች እየደረሰ ነው፡፡ የገጠር ኮሪደር ዋና ዓላማውም ገጠሩን በአሥተዳደር፣ በመሠረተ ልማትና በክትመት ሥርዓት በማስተሣሠር ወደ ከተማነት ማሳደግ ነው፡፡
በቀጣይ በከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረትን በተለያዩ አማራጮች ማቃለል፣ ጽዳትና አረንጓዴ ልማትን የሕዝብ ባሕል ማድረግ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ታሪካዊ ሃብቶችን ወደ ቱሪዝም ሃብትነት መቀየር፤ ወጣቶችን በዕውቀትና ክህሎት ለሥራ ማብቃት ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ለፎረሙ ስኬታማነት የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ያደረጋችሁ ሁሉ፣ በተለይም የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርን የአፋር ክልልና የሰመራ ሎጊያ ሕዝብና አሥተዳደርን በድጋሜ ማመስገን እፈልጋለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
