
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ሥልጠና ተጀምሯል።
በሥልጠና ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ብልጽግና ፓርቲ በየዓመቱ ሥልጠና የሚሠጠው የፓርቲውን ሃሳብ ለመሪዎች፣ ለአባላት እና ለማኅበረሰቡ ለማስረጽ ነው ብለዋል።
“ለውጥ የሚመራው በመሪ ነው” ያሉት ኀላፊው ለውጥን የሚመራ መሪ መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል። መሪን በተከታታይ ሥልጠናዎች ማብቃት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። ለውጥን በመፍጠር፣ በመፈጠን እና ሥራዎችን በጥራት በማከናወን መምራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በለውጥ ሂደት ውስጥ ያሉ ውጤቶችን ለማስገንዘብ፣ የሚገጥሙ ፈተናዎችንም በጋራ ለመፍታት ሥልጠናው አስፈላጊ መኾኑን ነው የገለጹት። መሪዎች ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመረዳት ምላሽ መስጠት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ሰፊ ሃሳብ ያለው፤ በሃሳብ የሚሠራ እና በሃሳብ የሚመራ ነው ብለዋል።
የሥልጠናው ዓላማ በመሪዎች መካከል የአስተሳሰብ አንድነት ለመፍጠር፣ መሪዎች ዕውቀት እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ በብልጽግና ፓርቲ እሳቤ ውጤታማነትን እንዲያረጋግጡ ለማስቻል ነው ብለዋል።
በመሪዎች መካከል አንድነት ሲፈጠር የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ ነው ያመላከቱት። ሀገርን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
