
ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ከጂኦ ስትራቴጂክ ኩስምና ወደ ላቀ ቁመና” በሚል መሪ መልዕክት ለአማራ ክልል ፖሊስ አመራሮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሠጠ ነው።
በሥልጠናው ማስጀመሪያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የጂኦ ስትራቴጂክ ጉዳይ የሀገራችንን ፖለቲካዊ ፍላጎት በምንፈልገው መልከዓ ምድር ላይ የምናስጠብቅበት መሣሪያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሚኖራትን የኀይል ሚዛን ለማስጠበቅ፣ በቀጣናው ያላትን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ፍላጎቷን ለማሳካትም ቁልፍ ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል።
ቀጣናው ካለው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አንጻር ከፍተኛ ዓለም ዓቀፋዊ ፉክክር የሚታይበት መኾኑንም አንስተዋል። ሀገራችንም ከዚህ ሁነኛ ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታዎች መገፋት የለባትም ነው ያሉት። ከዚህ እድልም መቋደስ ያስፈልጋታል ብለዋል። ለዚህም የጋራ አቋም እና ቁርጠኝነት መያዝ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በቀጣናው ተጽእኖ እንዳይኖራት የባንዳ ሆድ አደር እና የባዕዳን መሠሪ ተግባር እንቅፋት ኾነው መቆየታቸውን አንስተዋል። ይህንን ለማስተካከል ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እና አስተማማኝ የውስጥ ሰላም መፍጠር እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል። በሕግ እና በጠንካራ ዲፕሎማሲ ላይ የተመሠረተ የወደብ እና ተፈጥሮ ሀብታችንን የመጠቀም መብታችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል ነው ያሉት።
ይህንንም በእቅድ ለመምራት ይቻል ዘንድ የጂኦ ስትራቴጂክ ፖሊሲ እና እቅድ አዘጋጅታ እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ ገልጸዋል። ለስኬቱም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላም እና አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ይህንን ኀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮችን ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚገባመ አስገንዝበዋል።
ውስጣዊ ሰላምን ለማስፈን እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ሥነ ምግባር፣ ፍላጎት እና ብቃት ያለው ኀይል መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሉን የፖሊስ ኀይል ለማጠናከር እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የጠራ ግንዛቤ እና አቋም ለመያዝ የተዘጋጀ የሥልጠና መድረክ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
