የማርበርግ በሽታን ለመቆጣጠር ልዩ ክትትል እየተደረገ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

14
አዲስ አበባ: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ተከሰተ የተባለውን የማርበርግ ቫይረስ በተመለከተ የጤና ሚኒስቴር ለመገናኛ ብዙኀን ማብራሪያ ሰጥቷል።
ይህ በሽታ በዓለም ላይ የተገኘው እ.ኤ.አ በ1963 ጀርመን ማርበርግ ከተማ ነበር።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ የማርበርግ በሽታ ክስተት ተፈጠረ ከተባለበት ከኅዳር 3/2018 ዓ.ም ጀምሮ ተከታታይ መረጃዎች እየሰጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።
17 ሰዎች ላይ የናሙና ምርመራ መደረጉንም አስገንዝበዋል። ናሙና የተወሰደው ደግሞ ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች ላይ ጭምር መኾኑን ተናግረዋል።
ሕይወታቸው ካለፉ እና የምርመራ ናሙና ከተወሰደባቸው ስድስት ሰዎች ውስጥ ሦሥቱ ላይ የበሽታው ተጠቂ መኾናቸው እንደታወቀ ነው የተናገሩት። በበሽታው ሕይዎታቸው ላለፉ ሰዎችም ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ በጤና ማዕከሎች በማርበርግ ቫይረስ ተጠቂ የኾኑ ሰዎች የሉም ብለዋል።
ይህንን ምርመራ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም እና ላብራቶሪ ያረጋገጠችው መኾኗን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
የበሽታ ንክኪ ካለባቸው ሰዎች ላይ ልዩ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጤና ተቋማትን ጨምሮ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ልዩ ክትትል እያደረጉ ነው።
በአካባቢው ምልክቶች ሲታዩ ቶሎ ኅብረተሰቡ መረጃ እንዲሰጥ የጠየቁት ዶክተር መቅደስ ፈጥኖ ምላሽ የሚሰጡ የባለሙያዎች ቡድንም በአካባቢው ተሰማርቷል ብለዋል።
የመተላለፊያ መንገዱም በንክኪ በመኾኑ ምልክት ካላቸው ሰዎች ጋር ንክኪን መቀነስ እና የግል ንጽሕናን መጠበቅ ማኅበረሰቡ ሊከተላቸው የሚገባ መንገዶች መኾናቸውን ሚኒስተሯ አብራርተዋል።
አሁን ላይ ለጤና ባለሙያዎች ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ሥልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል። ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪም ወደ አካባቢው ተልኳል ተብሏል።
የሌሊት ወፍ ይህንን በሽታ አስተላላፊ በመኾኗ ከዚህች ጋር ሊኖር የሚችል ንክኪን መቀነስ፣ በሳኒታይዘር እጅን ማጽዳት እና መታጠብ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
በአካባቢው ከሚደረገው ክትትል ባለፈ በደንበር አካባቢ በዓለም አቀፍ እና በኢትዮጵያ የጤና ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ ልዩ ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚደረግ የኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ራሄል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሁለንተናዊ ብዝኀነትን ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠቀም ይገባል።
Next articleየተዘረጋው አሠራር ፈጣን እና ዘመናዊ በመኾኑ የመንግሥት አገልግሎቱን በቀላሉ ለማግኘት ያስችላል።