
ባሕር ዳር: ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል በባሕር ዳር ተመሥርቷል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ መንግሥት የመቻቻልና የአብሮነት ሀገር የኾነችው ኢትዮጵያን የተደማሪ ታሪክ እና ብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የነበሩ መለስተኛ ልዩነቶችን በመፍታት ሃይማኖቶች ተከባብረው እንዲኖሩ ማድረጉን አንስተዋል። የመንግሥት ጥረት ሰላም በመፍጠር እድገትና ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው፤ ታሪካችን ጠብቀን ትልቅ ሀገር ለመፍጠርም በጽናት እየሠራን ነው ብለዋል።
መንግሥት ሕዝቦች ነጻነታቸው እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ተከባብረው እንዲኖሩ እየሠራ ነው። የውጪ ባዕዳዎች አማራ ክልል ሰላም እንዲያጣ እየሠሩብን ስለኾነ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች ሊገነዘቡት እንደሚገባ አቶ ይርጋ አሳስበዋል።
ያጋጠመንን የውስጥ ግጭት ለመፍታት መንግሥት ያደረገውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ለክልሉ ሰላም እየሠሩ ነው፤ መላ የሙስሊሙ ማኅበረሰብም የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እንዲደግፍ እና ቅር ብሎናል የሚሉ ወንድሞችን በምክክር እና በውይይት ለአማራ ሕዝብ ሰላም ማግኘት እንዲተባበሩ እንፈልጋለን ብለዋል።
በሚቋቋመው የሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ወጣቶች አፍላ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን እና ዘመናዊነትን አዋሕደው ሀገራቸውን በማልማት እና ሰላም በማስፈን ድርሻውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የሃይማኖት አባቶችም እየተመካከሩ ስለ ሰላም እንዲሰብኩ እና ሰላም የሚነሱ ታጣቂ ኀይሎችን ወደ ሰላም እንዲመልሱ አሳስበዋል።
የለውጡ መንግሥት መገለጫ ልዩነትን በማክሰም እኩልነትን፣ ሰላምን እና አንድነትን ማስፈን ነው፤ ችግሮች ሲኖሩም ለሕዝብ እና ለሀገር የሚጠቅመውን ሃሳብ በማመንጨት ተወያይቶ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።
ካውንስሉ ሚዛናዊ፣ ለዜጎች ሰላም እና ደኅንነት አስቦ የሚሠራ እንዲኾን አሳስበዋል። የሃሳብ ልዩነቶችን በውይይት እና በምክክር የሚፈታበትን ልምምድ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን ሲሉም አሳስበዋል።
መንግሥት ሁሉንም የእምነት ተከታዮች ይደግፋል፤ በውይይት እና በምክክር ችግሮችን እንፈታለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን ባስተላለፉት መልዕክት የሙስሊም ወጣቶች ካውንስልን ለማቋቋም የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤቱ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ከሱስ የጸዳ እና በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ወጣቶች ላይ የመሥራትን ጠቀሜታ ጠቅሰዋል። የካውንስሉ ዓላማ ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለልማት መኾኑን በመገንዘብ ሕዝቡ እንዲደግፈው አደራ ብለዋል።
ሀገራችን የያዘችውን የባሕር በር ጥያቄ ለማሳካት ሁላችንም ከመንግሥት ጎን እንቁም ብለዋል።
ሁሉም አካላት ልዩነቶቻቸውን በውይይት ለመፍታት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላም እንዲመጡ አሳስበዋል።
መለያየት እና መጋጨት ውጤቱ ውድመት እና ውድቀት ነው፤ በመነጋገር እና በመተራረም ችግሮችን እንፍታ ብለዋል። መሣሪያ ይዘው የወጡ ወንድሞቻችን በሰላም ተመልሰው ከመንግሥት ጋር በልዩነቶቻቸው ላይ በመወያየት ሀገርን በጋራ ማልማት ይበጃልም ሲሉ ተደምጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
