
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የላቀ አፈፃፀም ላከናወኑ የፖሊስ አባላት እና መሪዎች ላሳዩት መልካም አፈፃፀም የእውቅና እና የማበረታቻ መርሐ ግብር አካሄዷል።
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ላለፉት 33 ዓመታት ከ130 ሺህ በላይ የፖሊስ አባላትን በተለያየ ሙያ አሠልጥኖ ወደ ሥራ በማሰማራት ለሕግ የበላይነት መከበር የበኩሉን አስተዋፅ እያበረከተ ያለ ትልቅ የሥልጠና እና የምርምር ተቋም ነው ያሉት የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ናቸው።
ላሳዩት የላቀ አፈፃፀም እንዲበረታቱ የተፈቀደላቸው የፖሊስ አባላት እና መሪዎች በቀጣይ የበለጠ የተጣለባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ አደራ ጭምር ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከሐምሌ 2017 ጀምሮ ከኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደረጃ እንዲያድግ መደረጉ ለተቋሙ ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሯልም ብለዋል። በተቋሙ አዳዲስ የሥልጠና መርሐ ግብሮችን በመቅረጽ ዋና የጥናት እና ምርምር ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ የሚገኝ ተቋም ነው ያሉት የደብረ ማርቆስ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ በጀመረው ሪፎርም ተቋሙ ዓለም አቀፋዊ ይዘትን ተላብሶ የማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ልምድ የሚወሰድበት እንዲኾን በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሀኑ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በሥነ ምግባር የተገነቡ እና ተልዕኮአቸውን በአግባቡ መወጣት የሚችሉ የፖሊስ አባላትን ለማፍራት የጀመረውን የሪፎርም ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ዘመኑን የሚመጥን አሠራር በመዘርጋት ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ሕዝቡ ከገጠመው የፀጥታ ችግር ማሻገር የሚችል ፖሊሳዊ ተቋም እንዲኾን በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።
የአማራ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በእውቀትእና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ብቁ የፀጥታ ኀይል በመገንባት እየተጋ ያለ ተቋም ነው ያሉት ደግሞ በዕውቅና ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁን ናቸው።
የፖሊስ አባላቱ ያገኙትን ማዕረግ ወደ ላቀ ተግባር በመቀየር እና ተልዕኮን በላቀ ቁርጠኝነት በመወጣት በክልሉ ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ መቋጫ እንዲያገኝ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአሳዩት አፈፃፀም እውቅና እና ማበረታቻ የተሰጣቸው የፖሊስ አባላት እና መሪዎች ያገኙት ማዕረግ እና እድገት የተሰጣቸውን ኀላፊነት አጉልተው በመወጣት ማኅበረሰቡ እያጋጠሙት ካሉ ችግሮች እፎይታ እንዲያገኝ በላቀ ደረጃ እንድንሠራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ተቋሙ በ1985 ዓ.ም ከማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተነስቶ አሁን ለደረሰበት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደረጃ እንዲደርስ ጉልህ ድርሻ ላበረከቱ ተቋማት እና የሥራ ኀላፊዎች ምስጋና ቀርቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
