
ባሕር ዳር: ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በኮምቦልቻ ለዘመናዊ አገልገሎት እና ለሰው ተኮር ተግባራት የተሰጠው ትኩረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ዛሬ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የዲጂታል አገልግሎትና የዘመናዊ የሥራ ቦታ እድሳትና ሰው ተኮር ተግባራትን ተመልክተናል ነው ያሉት።
የከተማ አሥተዳደሩ ሕንጻ የስማርት ሲቲ እሴቶችን ባሟላ መልኩ ታድሷል። ሕንጻው ዲጅታል አሠራርን ለመተግበር በሚያስችል መልኩ መደራጀቱ አገልግሎትን ለማዘመን አጋዥ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
ሌላው በከተማዋ የተመለከትነው በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች ተገንብተው ለነዋሪዎች የተላለፉ መኖሪያ ቤቶችን ነው፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ባለሀብቶችን እና ኅብረተሰቡን በማስተባበር ባስገነባቸው ሁለት የመኖሪያ ብሎኮች ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶችን አስረክቧል ብለዋል።
በኮምቦልቻ የጎበኘናቸው የዲጂታል የከተማ አገልግሎት ፕሮጀክትና ሰው ተኮር ተግባራት በከተሞቻችን እየተገበርናቸው ያሉ የአካታች ልማት ማሳያዎች ናቸው ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
