“ኢትዮጵያ በርካታ ማዕድን ያላት ግን በሚገባት ልክ ሳትጠቀም የቆየች ሀገር ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

2
አዲስ አበባ: ኅዳር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 4ኛውን የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ከፍተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤክስፖው የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ከዘርፉ አልሚዎች፣ ተመራማሪዎች እና ከነጋዴዎች ጋር እንዲገናኙ ያስችላል ብለዋል። “ኢትዮጵያ በገጸ ምድር እና በከርሰ ምድር የሚገኝ በርካታ የበለጸገ ማዕድን ያላት ግን በሚገባት ልክ ሳትጠቀም የቆየች ናት” ነው ያሉት።
የዘርፉን ስብራት በሚጠግን መልኩ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል መንግሥት በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የማዕድን ዘርፍ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለማግኘቷ የሚያስቆጭ እንደነበር ጠቅሰዋል።
አሁን ለዘርፉ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በተሰጠው ልዩ ትኩረት ከዘመናት ቁጭት ወደ ብስራት ተሸጋግራለች ነው ያሉት።
ባለሃብቶች በበርካታ የሀገሪቱ እምቅ እና ያልተነካ የማዕድን ሃብት ልማት እና እሴት ሰንሰለት በመሠማራት የውጭ ምብዛሬ እያስገኙ ነው ብለዋል። የሥራ ዕድሎችንም እየፈጠሩ መኾኑን ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ባለሃብቶች የተመቻቹ ፖሊሲዎችን፣ መሠረተ ልማቶችን እና የተቀላጠፈ የአገልግሎት አሰጣጥን ተጠቅመው ራሳቸውንም ኾነ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኤክስፖው ከኅዳር 4 እስከ 7/2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ተመላክቷል። የዘርፉ አምራቾች እና አቅራቢዎች፣ ተገናኝተው ምርት እና አገልግሎታቸውን እንደሚያስተዋውቁ ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ኢብራሂም ሙሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምርት እንዳይባክን በጥንቃቄ መሠብሠብ ያስፈልጋል።
Next articleየብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ብዝኅነትን በአንድነት፣ አንድነትን በብዝኅነት የምናሳይበት ልዩ ቀን ነው።