
ባሕር ዳር: ኅዳር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 4ኛውን ዓመታዊ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (MINTEX Ethiopia 2025) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ ምድሯም ልጆቿም ሃብታሞች ናቸው እስክንባል ድረስ ለአፍታም አንቆምም ብለዋል።
ዛሬ 4ኛውን ዓመታዊ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (MINTEX Ethiopia 2025) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከፍተናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ምድሯ ባለ ሦስት ድርብ ሃብት የያዘ ነው። የከርሰ ምድር ሃብቶች፣ የገጸ ምድር ሃብቶችን እና ልዩ የአየር ንብረትን ታድላለች ብለዋል።
ይህን ድልብ ሃብት ከነበረበት የመረሳት አባዜ በማላቀቅ ለሁለንተናዊ ብልጽግና ማሳኪያ ለመጠቀምና የኢትዮጵያን ዕድገት ለማረጋገጥ ጉዞ ጀምረናል ነው ያሉት።
መንግሥት የሰጠው ልዩ ትኩረትና የወሰዳቸው እርምጃዎች ለዘርፉ መነቃቃት እና ተስፋን በማምጣት በማዕድን ኢንቨስትመንትና ወጪ ንግድ ከፍተኛ እመርታን ፈጥረዋል።
ዓለም አቀፍ ኤክስፖው ባለድርሻ አካላትን፣ ባለሃብቶችን ፣ የቴክኖሎጂ አምራቾችን እና ምሁራንን በማሰባሰብ ያሉንን መልካም ዕድሎች የምናሳይበት እና ተግዳሮቶችን በቅንጅት የምንፈታበት ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
