
ባሕር ዳር: ኅዳር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ በነበረን ቆይታ የመኪና መገጣጠሚያ፣ የብርጭቆና የጠርሙስ ማምረቻዎችን ተመልክተናል ብለዋል።
በቆይታችን ያየናቸው ፋብሪካዎች የሀገር ውስጥ ግብዓትን በመጠቀምና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን እያዳኑ ነው።
ከብየዳ ጀምሮ ትላልቅ የኤሌትሪክ አውቶቡሶችን እየገጣጠመ የሚገኘው የፊቤላ ኢንዱስትሪያል መኪና መገጠሚያ በቀን 12 መኪና ማምረት የሚያስችል አቅም አለው፡፡ መገጣጠሚያው በቅርቡ ያስጀመረው አዲስ የቀለም መቀቢያ በርካታ ቀናትን ይወስዱ የነበሩ ሥራዎችን በሰዓታት ለማከናወን አስችሏል ነው ያሉት።
በአንድ ቀን 450 ሺህ ጠርሙስ የሚያመርተው ዴዴ ቦትል የብርጭቆና የጠርሙስ ማምረቻ ደግሞ 86 በመቶ የሚኾነውን ግብዓት ከሀገር ውስጥ ተጠቅሞ ለበርካታ የመጠጥ እና የመድኃኒት ፋብሪካዎች ጥቅም የሚሰጡ ጠርሙሶች ያመርታል ብለዋል።
በኢንዱስትሪዎቹ የተመለከትናቸው አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴዎች በየዘርፉ በጥራትና በፍጥነት በመትጋት የምናልመውን እድገት በአጠረ ጊዜ እንደምናሳካ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
መፍጠር፣ መፍጠን እና በጥራት መሥራት የሁልጊዜም የሥራ መመሪያችን ሊኾን ይገባል ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
