
ባሕር ዳር: ኅዳር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ”ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረውን 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን በባሕር ዳር ከተማ እያከበረ ነው።
በዓሉን አስመልክቶም በሕገ መንግሥት እና በፌዴራሊዝም ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ለክልል ሠራተኞች ግንዛቤ መፍጠሪያ ውይይት እየተደረገ ነው።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ አማካሪ ይርሳው ታምሬ በዓሉን በማክበር ሂደት የበዓሉን ዓላማ መገንዘብ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በዓሉ ሕገ መንግሥቱ የጸደቀበትን ቀን ታሳቢ ተደርጎ እንደሚከበርም ገልጸዋል።
ሕገ መንግሥት ሀገር የምትመራበት፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚረጋገጥበት መኾኑንም አንስተዋል። ሕገ መንግሥቱን በትክክለኛ ግንዛቤ በእምነት ይዞ መጠበቅ እንደሚገባም አንስተዋል።
የሕገ መንግሥቱን ይዘቶች እና የተዋረድ ሕጎች አውቆ በማክበር እና በመተግበር ዴሞክራሲያዊት እና ብዝኀነትን የምታስተናግድ ሀገርን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች እና መርሆዎች በመመራት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በጋራ የሚኖሩባት እና የሚገነቧት ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ቀኑን ማክበር ጠቀሜታው የጎላ መኾኑንም አንስተዋል።
ስለሕገ መንግሥት፣ የመንግሥት አወቃቀር እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመወያያ ሀሳብ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
