ሕጻናትን ከማንኛውም አይነት ጥቃት መከላከል ኀላፊነታችን ብቻ ሳይኾን ግዴታችን ነው። 

8

አዲስ አበባ: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ2024 በኮሎምቢያ ቦጎታ በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ማንኛውም አይነት ጥቃት ለማስቆም ኮንፈረንስ ተካሂዶ ነበር።

 

በዚህ ኮንፈረንስም ሀገራት በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም አይነት ጥቃት ለማስቆም ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

 

በዚህ መሠረትም ከአንድ ዓመት በኋላ የተገባውን ቃል ወደ ተግባር ለመቀየር የሕጻናት ጥቃትን መከላከል እና ምላሽ መስጠት አህጉራዊ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

 

ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው የቤተሰብ ኀላፊነት ጀርባቸው ላይ ይወድቃል። ይህም ያለ ዕድሜያቸው በሥራ እንዲሠማሩ፣ ባልተገባ እና ዕድሜአቸውን የማይመጥን ሥራ እንዲሠሩ ያስገድዳቸዋል።

 

ሕጻናት ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በድህነት፣ በመፈናቀል እና ሌሎች ምክንያቶች ለጥቃት ተጋላጭ ይኾናሉ።

 

ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቻርተርን ጨምሮ ሌሎች የሕጻናት መብትን ለማስከበር የገባቻቸውን ቃል ኪዳኖች በማክበር ሕጻናትን ከተለያዩ ጥቃቶች መጠበቅ እንደሚገባት የሕጻናት መብት ተሟጋች እና የሕጻናት ፓርላማ አባል ኢክራም ሲራጅ ተናግራለች።

 

ሕጻናት ሃሳባቸውን መግለጽ እንዲችሉ የሕጻናት ፓርላማ እና ሌሎች መድረኮች ሊሰፉ እንደሚገባም ጠቁማለች።

 

ሕጻናት የነገ ተስፋዎች በመኾናቸው ከጥቃት መጠበቅ እና መብታቸውን ብቻ ማስከበር ሳይኾን በአህጉራቸው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ሊደገፉ እንደሚገባም አስገንዝባለች። ለዚህ መሳካት ደግሞ የመማር መብታቸውን ማክበር ያስፈልጋል ነው ያለችው።

 

በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትቴር የሕጻናት መብት ጥበቃ ሥራ አስፈፃሚ ዘቢደር ቦጋለ ኢትዮጵያ

በ2024 በኮሎምቢያ ቦጎታ በተካሄደው ኮንፈረንስ

በሦሥት መሠረታዊ ጉዳዮች ቃል መግባቷን አስታውሰዋል።

 

የቤተሰብ የሕጻናት አስተዳደግን ለማሻሻል ፣ በሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለ ዕድሜ ጋብቻ ለመቀነስ እና የሕጻናት ጉዳይ አያያዝን ለማሻሻል ቃል የገባችባቸው ጉዳዮች እንደነበሩ አንስተዋል።

 

ቃል በተገባው መሠረት የሕጻናት አስተዳደግን ወደ 19 በመቶ ማሣደግ ተችሏል ብለዋል። ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና ግርዛትን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ እና ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የሕጻናት ጉዳይ አያያዝን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

 

ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ለሕጻናት ምቹ የኾነ ሀገር ለመፍጠር እና ሕጻናትን ለመጠበቅ የሚሠሯቸው ሥራዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ መኾናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ካስሎ ፍራንሲስ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

 

የሕጻናት መብት ለድርድር የሚቀረብ ጉዳይ ባለመኾኑ የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ከጥቃት ነጻ ኾነው፣ ጤናቸው ተጠብቆ እና አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጎላቸው ሊያድጉ ይገባል ብለዋል።

 

ሕጻናትን ከጥቃት ለመከላከል የፋይናንስ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን በማሟላት ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

 

ዘርፈ ብዙ ከኾነው የሕጻናት ጥቃት በተለይም በቤት፣ በትምህርት ቤት እና ሌሎች አካባቢዎች ከሚደርሱባቸው ጥቃቶች መጠበቅ እንዳለባቸው በኮንፈረንሱ ተገልጿል።

 

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) የሕጻናት መብታቸው እንዲከበር ከማንኛውም አይነት ጥቃት መከላከል ኀላፊነታችን ብቻ ሳይኾን ግዴታችን ነው ብለዋል። ሕጻናትን ከጥቃት ለመከላከል በቦጎታ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

 

ተጠያቂነትን በማረጋገጥ በሲቪል ሶሳይቲ፣ በግል ተቋማት፣ በኅብረተሰቡ እና በመንግሥት መካከል ጠንካራ ግንኙነት መገንባት ይገባል ነው ያሉት።

 

የሕጻናት፣ የወጣቶች እና ሴቶችን ተሳትፎ ያረጋገጠ ሥራ በመሥራት ጥቃትን መከላከል እና ምላሽ መስጠት ይገባልም ብለዋል።

 

ዘጋቢ፦ ሰላማዊት ነጋ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጫካ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ። 
Next articleየተፈራ ኀይሉ አጠቃላይ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ተጠየቀ።