
ባሕር ዳር: ኅዳር 2/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙትን የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርክ፤ የሴራሚክ ፋብሪካ እና የፐልፕ የወረቀት ፋብሪካዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት እነዚህ ግዙፍ ፋብሪካዎች በኢንዱስትሪ ዘርፍ የጀመርነው ሀገራዊ ሪፎርም እና ትግበራ ውጤት እየታየበት ለመሆኑ ህያው ምስክሮች ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በልዩ ትኩረት የያዘችው የአምራች ዘርፍ በባህሪው የሃብት ብዜት እና የዘርፎችን ትስስር የሚፈጥር እንደኾነም ተናግረዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን የተመለከትናቸው ፋብሪካዎች አምራች በመሆናቸው አዲስ ሃብትን ወደ ኢኮኖሚው ይደምራሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፎች ትስስርም የአንዱ ምርት ለሌላው ግብዓት የሚሆን እና በተለይ በሥራ እድል ፈጠራ እና የውጭ ምንዛሬን በማዳኑ በኩል ትልቅ ሚናን የሚወጡ ናቸው፡፡
ሰላም እና ትጋት ካለ ፋብሪካዎች ለልማት፤ ዜጎች ለለውጥ ሃገርም ወደ ዘላቂ ብልጽግና እንደምትራመድ የሰሜን ሸዋ ዞን ማሳያ ናት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
