
አዲስ አበባ: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ሲቢኢ በጄ “የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲስ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎትን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ አገልግሎት እየሰጠ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በ2017 ዓ.ም ከ17 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር እና ክፍያ በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች በቀላሉ መፈጸም ተችሏል ብለዋል።
በጥሬ ገንዘብ መጠቀምን በመተው ወደ ዲጂታል አማራጭ መሄድ ሀገራዊ ስትራቴጂ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል አገልግሎቶቹን ተደራሽነት በማስፋፋት እና በማሳደግ ለሌሎች የፋይናንስ ተቋማት አርዓያ መኾን ችሏል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዲጂታል የባንክ አማራጮች መካከል የአብዛኛውን ማኅበረሰብ አቅም እና ፍላጎት ያማከለ “ሲቢኢ በጄ” የተሰኘ በዲጂታል የታገዘ የብድር እና ቁጠባ አገልግሎትን ለሕዝብ ማቅረቡንም ተናግረዋል።
“ሲቢኢ በጄ” የዲጂታል ባንክ አገለልግሎት ለመንግሥት ሠራተኞች ቅድሚያ ሰጥቶ ተጠቃሚ ለማድረግ የመጣ መኾኑን አስታውሰዋል። አገልግሎቱ ባንኩን ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር እና ኅብረተሰቡንም በቀላሉ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩም ተጨማሪ የብድር አገልግሎቶችን እና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት አማራጮችን ለኅብረተሰቡ ቀልጣፋ እና ምቹ በኾነ መንገድ ለማቅረብ በርካታ ሥራዎች እየሠራ መኾኑም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
