
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ መልዕክት ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ መሪዎች ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቅቋል።
ከጥቅምት 19 እስከ 30 2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ መሪዎች ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰጡት የሥራ መመሪያ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ ወደ 2ሺህ የሚጠጉ የፓርቲው መሪዎች የተሳተፉበት፣ የአስተሳሰብ አንድነት ከመፍጠር እና የተግባር አፈጻጸምን ከማላቅ አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ በተገኘበት በዚህ ሥልጠና ፓርቲያችን እውነተኛ የኅብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት መኾኑም በተጨባጭ የተንጸባረቀበት ነበር ብለዋል።
ይህ የሥልጠና መርሐ ግብር ከዝግጅት እስከ ገለጻ፣ የቡድን ውይይት፣ ተሞክሮ ልውውጥ፣ የልማት ሥራዎች የመስክ ጉብኝት እና ማጠቃለያ ድረስ ዓላማውን በሚገባ አሳክቶ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታችሁን ለተወጣችሁ በሙሉ ላበረከታችሁት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
