
አዲስ አበባ: ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ ኅብር የ20 ዓመታት የሥራ አፈጻጸም እና የቀጣይ ሥራዎችን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው::
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በ1987 ዓ.ም በሕትመት የሚዲያ ዘርፍ ሥራውን የጀመረ ሲኾን ከምሥረታው 10 ዓመታት በኋላ ደግሞ በ1997 ዓ.ም በክልሉ የሚነገሩ ሦስት ቋንቋዎችን ማለትም በአዊኛ፣ በሕምጣና እና በኦሮሚፋ ቋንቋዎች ሥርጭት የጀመረ የሕዝብ ሚዲያ ነው።
የምክክር መድረኩን ያስጀመሩት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥራ አሥፈጻሚው አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ ናቸው። አሚኮ የዛሬ 30 ዓመት በጥቂት ሰዎች ሥራውን በሕትመት ዘርፍ የጀመረ ተቋም ነው ብለዋል።
አሁን ላይ በሁለት የቴሌቪዥን ቻናሎች፣ በሰባት የኤፍ ኤም ጣቢያዎች እና በ12 ቋንቋዎች ስርጭቱን እያስተላለፈ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም እንደኾነም ነው የተናገሩት። ከዚህ በተጨማሪም በአራት ቦታዎች የቴሌቪዥን የቀጥታ ዝግጅት እያቀረበ ያለ ሚዲያ ነው ብለዋል
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በቀጣይም ተደራሽነቱን የማስፋፋት ሥራዎችን እየሠራ ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ደሴ ትልቅ የሚዲያ ኮምፕሌክስ እየተገነባ እንደኾነም ተናግረዋል። አዲስ አበባ ላይም ትልቅ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ለመገንባት የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነም ገልጸዋል።
ባለፉት 30 ዓመታት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን እየዳሰሰ ለዓመታት የተጋ ሚዲያ እንደኾነ ያነሱት አቶ ግዛቸው “የብሔረሰብ ዞኖች ባሕል እና ቋንቋዎች እንዲያድጉ ሠርቷል፤ እየሠራም ነው” ብለዋል::
አሚኮ በተለያዩ ደግ እና ክፉ ጊዜ ከሕዝብ ጋር የቆመ ሚዲያ ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ትላልቅ በጀቶችን በመመደብ ጭምር በክልሉ በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎች በአዊኛ፣ በሕምጣና እና ኦሮሚፋ ቋንቋዎች ልዩ የበዓል ዝግጅቶችን ሽፋን እየሰጥ እንደሚገኝም ለአብነት አንስተዋል።
በቀጣይ በርካታ ማስፋፊያዎችን ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ለዚህም ማሳያው ሰቆጣ ላይ የኤፍ ኤም ማሠራጫ ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው፤ እንጅባራ ላይም የኤፍ ኤም ግንባታ ለመጀመር እንሠራለን ነው ያሉት።
በመድረኩ የሦስቱ ቋንቋዎች ማለትም የአዊኛ፣ የሐምጣና እና የኦሮሚፋ የ20 ዓመታት ጉዞ መነሻ ጽሑፎች ቀርበዋል።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
