ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ተቋማዊ እና መንፈሳዊ ሞዴል ሀገር ናት፡፡

0
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከሰው ዘር መገኛነቷ ባሻገር ለዓለም ጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነጻነት ትግል ፋና ወጊ ቀንዲል ናት፡፡ የዓድዋ ድል አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ጭቆና እና ብዝበዛ እንድትላቀቅ የማንቂያ ደወል ኾኖ አገልግሏል፡፡
ከፖለቲካዊ ነጻነት ማግስት ለሚጠበቀው አሕጉራዊው የምጣኔ ሃብታዊ ነጻነትም ኢትዮጵያ ተጠቃሽ እና ሞዴል ሀገር ናት፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ነው፡፡
ከሞላ ጎደል ቀጥተኛ ከኾነ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ነጻ የኾነች አሕጉር ለመመሥረት የተደረገው ጥረት መነሻውም መዳረሻውም ጥንታዊቷ እና ምሥራቅ አፍሪኳዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡
ዛሬም ድረስ “አፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” ያገኙ ዘንድ ኢትዮጵያ ለአሕጉሩ ሀገራት መሠባሠቢያ ጥላ ናት፡፡ ታዲያ አሁን ላይም አፍሪካ ለምትሻው ምጣኔ ሃብታዊ ነጻነት የኢትዮጵያ ሚና እና አበርክቶ የላቀ እንደኾነ ይነገራል፡፡
ለአሕጉሩ ሀገራት ንቀት እና የተሳሳተ ትርክት አራማጆች ሠርቶ ከማሳየት የተሻለ አማራጭ የለም ያሉት የአውሮፓ ኅብረት እና የምዕራብ ሀገራት የኢትዮጵያ ፓርላማ ወዳጅነት ቡድን ሠብሣቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አፍሪካ ትችላለች የሚለውን እሳቤ ለማሥረጽ ኢትዮጵያ እያሳካቻቸው ያሉት ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡
አሕጉራዊ ተምሳሌት ከኾኑት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ አንዱ ማሳያ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከትናንት እስከ ዛሬ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ተቋማዊ እና መንፈሳዊ ሞዴል ናት ያሉት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የግድቡ መጠናቀቅ እና መመረቅ አሕጉራዊ ትርጉሙ ቀላል አይደለም ነው ያሉት፡፡
አሕጉሪቷ የምትሻውን ምጣኔ ሃብታዊ ነጻነት ለመቀዳጀት ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ዕውን አድርጎ ማሳየት ይጠይቃልም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በግድቡ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያበሰሯቸው የታላላቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ አሕጉራዊ መሪነትን እና ተሰሚነትን የሚያሳድጉ እንደኾኑም አንስተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እና ገንዘብ ተጠናቅቀው ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ውስጣዊ ሰላምን እና አንድነትን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አምባሳደር ዲና የውስጥ አቅምን ማጠናከር፣ በጋራ መቆም እና በታናናሽ አጀንዳዎች ከመጠመድ በመውጣት ሀገራዊ መልክ እና ቁመና ላይ ማተኮር ይገባልም ብለዋል፡፡
ትናንት ለአፍሪካ ሀገራት ፖለቲካዊ ነጻነት ምሳሌ የኾነችው ሀገር ዛሬም ለአሕጉሪቷ ምጣኔ ሃብታዊ ነጻነት ምሳሌ ለመኾን በራስ አቅም እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በትብብር እና በጋራ ማጠናቀቅን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የባሕር በር ጥያቄን ጨምሮ ሌሎች ብሔራዊ ጥቅም ላይ የተመሠረቱ ጉዳዮችን በባለቤትነት መንፈስ መያዝ እና መፈጸም እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበሰላም ተንቀሳቅሶ ሕይዎትን ለመምራት እንቅፋቶችን በጋራ መከላከል ይገባል።
Next articleየኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል።