“የማትረሳ ዕለት፤ የማይደገም ድርጊት”

28
ባሕር ዳር: ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ያቺን ዕለት ኢትዮጵያውያን አይረሷትም፤ ከልባቸው መዝገብ ላይ አይፍቋትም፤ ከትውሳታቸው ማሕደር ላይ አይሰርዟትም፤ ሁልጊዜም እያስታወሷት፤ ሁልጊዜም እያሰቧት፤ መጥፎ ሃሳብን እና ክፉ ድርጊትን እያወገዙባት ይኖራሉ እንጂ።
ያቺ ዕለት ያመነ የተከዳባት፤ የደገፈ የተገፋባት፤ ያጎረሰ የተነከሰባት፤ የተጠማን ያጠጣ ለጉሮሮው ቀዝቃዛ ውኃ የተከለከለባት፤ የታረዘን ያለበሰ የተራቆተባት፤ በመከራ ቀን አብሮ የቆመ እንደ ጠላት የታየባት፤ ለሠንደቅ ዓላማ ክብር የቆመ እንደ ጠላት የተቆጠረባት፤ ለዓመታት ከምሽግ ሳይወጣ የጠበቀ ወገኖቼ ባላቸው በክፋት ጦር የተወጋባት፤ ከፊት ሲጠብቅ ከኋላ የተመታባት ናት።
በዚያች ዕለት ያለ ጥርጥር ያመኑ ባመኑት ተክደዋል፤ በምሽግ ውስጥ ኾነው ሀገር የጠበቁ በጠበቁት ወዳጅ ተገድለዋል፤ ለደስታው ሲሉ መከራን በተቀበሉለት ሰው በጀርባ ተወግተዋል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ሕወሀት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት የፈጸመባት ቀን ናት። ይህም ክህደት ከክህደት የከፋ እና ፈጽሞ ሊደገም የማይገባው ድርጊት ነው።
“ፍቅር ታረደ አሉ ውሻ ደሙን ላሰው
ከእንግዲህ ሆድ ለሆድ አልተገናኘም ሰው” እንዳለ የሀገሬው ጠቢብ በዚያች ቀን መተማመን ሞታለች፤ ፍቅር በጨካኞች ጦር ተወግታለች፤ ቃል ኪዳን በጨካኞች ሰይፍ ተቆርጣለች።
በዚያች ዕለት ኢትዮጵያ ስለ ልጆቿ ደም ደምታለች፤ ስለ ልጆቿ እንባ አንብታለች፤ በልጆቿ ላይ ስለ ተፈጸመው ግፍ አዝናለች፤ ስለ ልጆቿ መንከራተት ልቧን አድምታለች።
ነገር ግን ስለ ፍቅር ብላ ይቅርም ብላለች፤ አብሮ ለመኖር ስትል እንደ እናት ያለፈውን ትታለች፤ ሀዘኑ መራር፤ ድርጊቱም የከፋ ቢኾንም እናት ናትና ሁሉን በልቧ ይዛ ለልጆቿ ስትል ትታለች። እዳይደገም ግን ቀኗን ታስባለች። ድርጊቱንም ፈጽማ ታወግዛለች።
ያቺ ዕለት አትረሳም፤ ያ ድርጊትም አይደገምም። ስለ ምን ቢሉ ክፉ ድርጊት የተፈጸመባት እና ጥቁር ጠባሳ የጣለች ናትና። ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቀኗን እያሰቧት ድርጊቱንም እያወገዙት ይኖራሉ።
፶ አለቃ ጋሻዬ ጤናው የተካደው ሰሜን ዕዝ በተሰኘው መጽሐፋቸው ሠራዊቱ የመጨረሻው የግፍ ጽዋ እንዲጎነጭ የክህደት ጥይት ከተተኮሰበት ቀን ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም አስቀድሞ በርካታ ግፎች ይፈጸሙበት እንደነበር ጽፈዋል።
የሕወሃት ሰዎች በሃሳብ የበለጧቸውን፣ በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸውን፣ ለሀገር እና ሕዝብ የሚጠቅም ለየት ያለ ሃሳብ የሚያቀርቡ፣ የተማሩትን እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የኾኑ ሰዎችን ኾን ብሎ የወንጀል ወጥመድ በማዘጋጀት እስር ቤት መክተት፣ አለበለዚያም የተለያየ ምክንያት በመፍጠር ማሰናበት ዋነኛ መለያቸው ነበር ይላሉ።
ይህ ሴራቸው በመከላከያ ሠራዊቱ ዘንድ በጥንቃቄ እና በሰፊው የሚሠራበት ድብቅ ግን ደግሞ በይፋ የሚታወቅ አስነዋሪ ጸባያቸው ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉት ስጋት እና ፍርሀት ስላለባቸው ነው፡፡ ሠራዊቱን እንደፈለጉ ማድረግ ስለሚፈልጉ እንደ እነዚህ ዓይነት ግለሰቦች “አሻፈረኝ” ሊሉ ይችላሉ፤ ሌላው ሠራዊትም በቀላሉ ሊከተላቸው ይችላል የሚል ፍርሃት እንቅልፍ ይነሳቸዋል ነው የሚሉት።
በዚህ ተንኮላቸው ከታችኛው ሠራዊት ወጣት ወታደሮችን በሰበብ አስባብ በወንጀል አመካኝተው ለዓመታት እስር ቤት እንዲማቅቁ አድርገዋል ብለዋል በመጽሐፋቸው። ለሀገራቸው ብዙ በሚሠሩበት የአፍላ ዕድሜያቸው የሚወዱትን ውትድርና እና ለሀገር የማገልገል ስሜት ትተው በግድ ከሠራዊቱ ያለ ምንም የአገልግሎት ክፍያ እንዲሰናበቱ አድርገዋል ይላሉ።
ሕወሃት በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ አስቀድሞ በርካታ ዝግጅቶችን አድርጓል፤ የሰሜንን ዕዝ ከመታሁ ኢትዮጵያን መልሼ እቆጣጠራለሁ የሚል ተስፋ እና ምኞትም ነበረው።
እሳቸው ሲጽፉ ሕወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንደኛው በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተጀመረው ሪፎርም ነበር ይላሉ።
“በመከላከያ የተደረገው ሪፎርም ሕወሃት ጥቅምት 24 በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው። ይህ ሪፎርም በመከላከያ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሠራዊቱ መሪዎችን በእጅጉ ጎድቷል።
ምክንያቱም ከታች እስከ ላይ የያዙት እነርሱ ስለነበር ነው። የሕወሃት ሰዎች እንዳሻቸው የሚጫወቱበት እና የሚንፈላሰሱበት ማላገጫቸው ተቋም ነበር መከላከያ። ሪፎርሙ ይህን የምቾት ወንበራቸውን ነቀነቀባቸው፡፡ እንዳሻቸው የፈለጉትን ይሠሩበት የነበረውን ዕድላቸውን ነጠቃቸው” ነው የሚሉት።
የሰሜን ዕዝ በእነዚህ ምክንያቶች እና በሌሎች ተከዳ። ዓይኑን እርግብ ሳያደርግ ለዓመታት በጠበቀው አካባቢ ከጀርባው ተወጋ። በዚያ ጥቃት በርካታ የሠራዊት አባላት ተሰውተዋል፤ ብዙዎች ቆስለዋል፤ የሠራዊት ቤተሰቦች እና ከሞት የተረፉ አባላት አሰቃቂ ግፍን በዓይናቸው ተመልክተዋል። በዚያ ግፍ አያሌ ኢትዮጵያውያን አልቅሰዋል፤ በእልህ እና በቁጣም ተነስተዋል።
አሰቃቂ ግፍ እና ክህደት የተፈጸመበት ሠራዊቱ አንገቱን ደፍቶ እና አዝኖ አልተቀመጠም። ራሱን አደራጅቶ የካዱትን ቀጣቸው፣ በሀገር ሉዓላዊነት እና የመጨረሻው ምሽግ ላይ የተነሱትን በክንዱ አንበረከባቸው፤ የማይጨበጥ ነበልባል፤ የማይሸነፍ ክንደ ብርቱ መኾኑንም አሳያቸው እንጂ።
ጥቅምት 24 በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያውያን ያን ክፉ ድርጊት ያስቡታል፤ እንዳይደገምም ያወግዙታል። እነኾ ዛሬ ጥቅምት 24 ናት። ያቺ የግፍ ግፍ የተፈጸመባት፣ ያመነ የተካደባት፤ ድጋሜ ሊታሰብ የማይገባው ድርጊት የተደረገባት ናትና እየታሰበች ነው።
ቀኗ ስትታሰብ ለሀገር ክብር እና ፍቅር ታምነው የወደቁ ጀግኖች ይታሰባሉ፤ ቀኗ ስትታወስ እስከ መቃብር ድረስ የታመኑ ጀግኖች ይታወሳሉ፤ ቀኗ ስትዘከር ታምነው ሳለ የተካዱ፤ ለራሳቸው ሳይኾን ለሌላ የኖሩ ልበ ሙሉዎች ይዘከራሉ።
ቀኗ ስትታወስ የደረሰባቸውን አካላዊ፣ አዕምሮዓዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ተቋቁመው የካዳቸውን የቀጡት፤ የሀገር ሉዓላዊነትን ያስከበሩት፣ ሀገርን ከመፍረስ፣ ሕዝብንም ከመበተን ያዳኑት ጀግኖች ይታወሳሉ፤ ከፍ ከፍም ይደረጋሉ። በታሪክ እና በትውልድ ይከበራሉ።
ሀገር የመጨረሻ አለኝታዋ እና መከታዋ ሠራዊት ነው። ሠራዊትን የነካ ሀገርን የነካ ነው። ሠራዊትን ያጠቃ ሀገር እና ሠንደቅ ዓላማን፤ ክብር እና ሉዓላዊነትን፤ ነጻነት እና ማንነት የሚያጠቃ ነው። ይህን ያደረገ ሁሉ ሀገር ላይ የተነሳ ነው።
ሠራዊት የሌላት ሀገር የጠላት መናኸሪያ ትኾናለች፤ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ጀግና ሠራዊት ያላት ሀገር ደግሞ ከውጭ እና ከውስጥ ጠላቶች ተጠብቃ ትኖራለች፤ ከሩቅም ከቅርብም የሚነሱ ጠላቶቿን እየቀጣች፤ በክብር እና በነጻነት ትኖራለች።
ኢትዮጵያ ችግር የማይበግራቸው፤ ፈተና የማይጥላቸው፤ መገፋት እና መከዳት ከእርምጃ የማያስቆማቸው የጀግኖች ምድር ናት። በጀግኖች እንደተጠበቀች፤ በጀግኖች እንደተከበረች ትኖራለች። ጀግኖችን ያከበረ ሀገሩን ያከብራል፤ ጀግኖችን ያሰበ ሀገሩን ያስባል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።
Next articleየጠራ አቋም በመያዝ ባንዳዎችን እና ባዕዳዎችን መመከት ይገባል።