
ባሕር ዳር: ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጥቅምት 24 በሰሜን ዕዝ የተፈጸመው ድርጊት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ታስቧል።
የሰሜን ዕዝ ዝክረ ሰማዕታትን ለመዘከር በተዘጋጀው የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሠራዊቱ ከየትኛውም አቅጣጫ በየትኛውም ጊዜ በልማታችን ፣በሰላማችን እና በብሔራዊ ጥቅማችን ላይ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ ነው ብለዋል።
ከሃዲው ሕወሃት መከላከያ ሠራዊት ለሀገሩ ክብር የከፈለውን መስዋዕትነት ክዶ ኢ ሰብዓዊ በኾነ መንገድ ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ የኾነ ግፍና ጭካኔ መፈጸሙን አስታውሰዋል።
ይህ ድርጊት መላው ሠራዊቱን እና መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሳዘነ እና አንገት ያስደፋ እንደነበር አንስተዋል። “መቼም የትም እንዳይደገም መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ መልዕክት ቀኑ በልዩ ሁኔታ መታሰቡንም ገልጸዋል።
ሰውን በዘረኝነት እና በጥላቻ ቀስቅሰው እና አነሳስተው ከጠላት ተዋግቶ ነፃ ያወጣውን፣ አንበጣ እያባረረ ሰብል የሚሰበስበውን አምኖ ደክሞት ያረፈውን የመከላከያ ሠራዊት በተኛበት ክህደት መፈፀማቸው በጣም ያማል ብለዋል።
ይህ ድርጊት በተፈፀመበት ወቅት የኢትዮጵያ ሠራዊት ተገዶ የሕልውና ዘመቻ በጀመረበት እና ትግራይ ውስጥ በገባበት ወቅት አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ሠራዊቱ እንደተበደለ እና እንደተካደ ያውቅ ስለነበር ከሠራዊቱ ጎን ይቆም እንደነበርም አስታውሰዋል።
ዛሬም ቢኾን ይህ የከሃዲዎች ስብስብ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ከማስጠበቅ ይልቅ ትላንትና እታገልልሃለሁ ብሎ ልጆቹን ከጉያው ነጥቆ እየወሰደ አስጨፍጭፎ ባዶውን ያስቀረውን የትግራይን ሕዝብ ከመካስ ይልቅ ዳግም ለሌላ እልቂት እየተዘጋጀ እና የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል ብለዋል።
ከሀገር መከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ እንደሚታመላክተው መላው የትግራይ ሕዝብ ትላንትና የደረሰበት መከራ ዛሬም እንዳይደገም በቃ ሊልና ራሱን ነፃ ሊያወጣ ይገባዋል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		