
አዲስ አበባ: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንሰሳት ሃብት ልማት እና የእንስሳት ተዋጽዖ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ እና ዐውደ ርዕይ ተከፍቷል።
ከ14 ሀገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ ዓለም ዓቀፍ የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ተዋናዮች፣ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሀገራት አምባሳደሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና የንግድ ጎብኝዎች በመከፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር አማካሪ ዓለማየሁ መኮንን (ዶ.ር) ዐውደ ርዕይ እና ጉባኤው የእንስሳት ሃብት የገበያ ሰንሰለቶች ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ትውውቅ፣ የገበያ ትስስር እንዲሁም የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበት መኾኑን ተናግረዋል።
የኔዘርላንድ አምባሳደር ክሪስቲን ፒረኒ ኔዘርላንድ የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት በዕውቀት፣ በቴክኖሎጅ እና በገበያ ትስስር እንዲመራ ልምዷን በማካፈል ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
መሠረቱ ኢትዮጵያ የኾነው የፕራና ኤቨንትስ ድርጅት ዳይሬክተር ነብዩ ለማ በዐውደ ርዕዩ ከ14 ሀገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ የዘርፉ ድርጅቶች እየተሳተፉ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ዶሮ ኤክስፖ፣ የአፍሪካ የእንስሳት ሃብት ዐውደ ርዕይ እና ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ የአሳ ኤክስፖ እና የኢትዮጵያ የማር ኤክስፖዎችም በዚሁ ዝግጅት እየተካሄዱ መኾኑን አስረድተዋል።
ኹነቱን ከ5ሺህ በላይ የኢትዮጵያ፣ የምሥራቅ አፍሪካ እና ዓለም አቀፍ ሀገራት ጎብኝዎች እንደሚጎበኙትም አስረድተዋል።
ዐውድ ርዕዩ በሚሊኒየም አዳራሽ ከጥቅምት 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦሥት ቀናት ቆይታ እንዳለው ተነግሯል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		
