‎ለማር ምርት ጥራት ይጠነቀቃሉ ?

13
ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በአማራ ክልል የንብ ሃብት ጸጋ አለ። ማር በሁሉም የክልሉ አካባቢዎችም ይመረታል፡፡
ማር ባለው ተፈጥሯዊ የምግብነት እና መድኃኒትነት ይዘት በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይሁንና ብዙ ጊዜ ከማር ምርቶች ላይ የጥራት ችግር ይስተዋላል፡፡
የጥቅምት ወር ማር የሚቆረጥበት ወይም የማር ምርት በስፋት የሚሰበሰብበት ወቅት ነው፡፡ ጥራት ያለው የማር ምርት ለማግኘት ደግሞ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
‎አቶ መልካሙ ይግረመው በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ማር በማምረት ሥራ ላይ ተሠማርተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ 400 የሚደርሱ የንብ ቀፎ እንዳላቸውም ነግረውናል፡፡ የሚያመርቱትን ማር ጥራት ጠብቀው ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል፡፡
‎ማር በሚቆርጡበት ጊዜ የሚጠቀሙባቸውን ዕቃዎች ንጹሕ እና ከምንም ንክኪ ነጻ መኾናቸውን አንስተዋል። ከኩበት ጭስ ይልቅ የጤፍ ገለባ ጭስ እንደሚጠቀሙም ተናግረዋል፡፡
ይህም የማሩ ጣዕም እንዳይቀይር ያደርጋል ብለዋል፡፡ ማሩም ከተቆረጠ በኋላ በማጣራት ሠሙን በመለየት ለየብቻ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ነው የገለጹት፡፡
‎የተጣራውን ማር ንጽሕናውን በጠበቀ እና ለማር ማስቀመጫ የሚኾኑ የፕላስቲክ ዕቃዎችን ተጠቅመው ለተጠቃሚ እንደሚያቀርቡ ነው የገለጹት፡፡
‎ሌሎች ማር አምራቾችም ማር በሚቆርጡበት ጊዜ ንጽሕናውን በመጠበቅ እና ማሩን በማጣራት ጥራት ያለው ምርት ለተጠቃሚ ማቅረብ ይቻላል ነው ያሉት፡፡
‎በአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ የንብ እና ሐር ልማት ከፍተኛ ባለሙያ ሙሐመድ ጌታሁን የማር ምርት ጥራት ለማስጠበቅ በሚቆረጥበት ጊዜ ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ አለበት ይላሉ፡፡
‎ማር ለመቁረጥ የመጀመሪያው ነገር የሚቆረጠው የማር እንጀራ ከ75 በመቶ በላይ በሰም መታሸግ አለበት ይላሉ፡፡ በሰም ሳይታሸግ አይኑ እንደተከፈተ ከኾነ ማር ሳይኾን ያልበሰለ የአበባ ወለላ ነው ብለዋል።
ቢቆረጥም ገና ወደ ማር ያልተቀየረ ስለሚኾን ጥራት አይኖረውም፤ ለሌላ የመብላላት ሂደት ስለሚጋለጥ ይበላሻል ነው ያሉት፡፡ በሰም ካልታሸገ ጊዜው ገና በመኾኑ ተጨማሪ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
‎የደረሰ ማር በሚቆረጥበት ጊዜ የሚጠቀሙባቸው ዕቃዎች ንጹሕ እና ደረቅ መኾን እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡ ማር ፈጽሞ ከእርጥበት ወይም ውኃ ጋር ሊገናኝ አይገባም ነው ያሉት፡፡
ማር የሚቆረጥበት እና የሚቀመጥበት እቃም ለምግብ ማስቀመጫነት የተፈቀደ መኾን አለበት ነው ያሉት፡፡ በቀለም ወይም ሌሎች የኬሚካል ማስቀመጫ የነበሩ ዕቃዎችን መጠቀም እንደሌለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
‎ማር ከሚቆርጠው ሰው የግል ንጽሕና ጀምሮ ቢላዋ እና ሌሎች ዕቃዎችንም በንጽሕና ይዞ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በሚቆርጡበት ጊዜ ከኩበት ጭስ ይልቅ ጥሩ መዓዛ ያላቸውን፣ ቀለል ያለ ጭስ እንደ ወይራ፣ የበቆሎ አገዳ እና ጭድ መጠቀም ይመከራል ብለዋል፡፡
‎ማር ከተቆረጠ በኋላ የማር መጭመቂያ ወይም ማጣሪያ በመጠቀም ንጽሕናውን መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ማጣራት ማለት ማሩን ከሰሙ መለየት ማለት ነው፡፡ የተጣራውን ማር ለምግብ ማሸጊያ በተፈቀዱ የፕላስቲክ ወይም የብርጭቆ ዕቃዎች በመጠቀም ለተጠቃሚ ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
‎ማር ካልተጣራ ሰሙም ማሩም ተደበላልቆ ነው የሚሸጠው ያሉት ባለሙያው ከተጣራ ግን ማሩ እና ሰሙ ለተፈለጉበት ዓላማ ይውላሉ ነው ያሉት፡፡
‎ማር እርጥበት እና ሽታን የሚስብ በመኾኑ ለብክለት ይዳርጋል፤ ስለዚህ ሲቀመጥ በንጹሕ እና መጥፎ ሽታ በሌለበት ደረቅ ቦታ መኾን አለበት ይላሉ፡፡ ማር እርጥበት እና የንጽሕና ጉድለት ሲኖረው ሽታው ይቀይራል፣ ጣዕሙም ይበላሻል፤ ሰዎችን በረጅም ጊዜ ሂደት ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል ነው ያሉት፡፡
በተለይም አርሶ አደሮች ማርን በማዳበሪያ ማስቀመጥ የተለመደ ነው፤ ነገር ግን ይህ ፈጽሞ መደረግ የለበትም ብለዋል፡፡
‎በክልሉ ያለውን የማር ምርት አሰባሰብ ሂደት ለማሻሻል ሙያዊ ድጋፍ በባለሙያዎች እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ያልተሻሻሉ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ማር ማጣራት ባለፉት አምስት ዓመታት እየተሻሻለ ቢኾንም አሁንም ሥራን የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
‎ማር አምራቾች ጥራት ያለው ምርት ለተጠቃሚ ለማቅረብ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እና ትክክለኛውን የአቆራረጥ ዘዴ መከተል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊ እና የሕዝብ ድጋፍ ያለው ነው።
Next articleበእንሰሳት ሃብት ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እና ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ።