የማኅበራዊ ሚዲያ እና የክላውድ ደኅንነት

7
ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምንጠቀምባቸው የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች እጅግ በጣም ብዙ መጠን ያለውን የተጠቃሚ መረጃ የማቀናበር እና የማሥተዳደር ሥራቸው በዋነኝነት የሚመሠረተው በክላውድ ቴክኖሎጂ ላይ ነው።
የክላውድ አገልግሎት ማለት በበይነ መረብ ትስስር በመፍጠር መረጃን ሌሎች ትላልቅ ኩባንያዎች ባዘጋጇቸው ኮምፒውተሮች ላይ ተከራይቶ ማስቀመጥ የሚቻልበት አገልግሎት ነው፡፡
በተጨማሪም በእኛ ኮምፒውተሮች ላይ መተግበሪያዎችን መጫን ሳይጠበቅ የክላውድ አገልግሎት የሚሰጡ ኮምፒውተሮች ላይ የተጫኑትን ኦንላይን በሚኖር ግንኙነት እንድንጠቀም ይረዳናል፡፡
ትልቅ አቅም ያለውን ኮምፒውተር ወይም ማከማቻ ቋት ከመግዛት ይልቅ አገልግሎቱን በኪራይ ወይም ያለክፍያ መጠቀም ያስችላል። በቀላሉ ለመረዳት በጂሜይል የምንለዋወጠው መረጃ የሚቀመጠው በእኛ ኮምፒውተር ሳይኾን በጉግል ክላውድ ላይ ነው፡፡
የክላውድ ደኅንነት ማለት የክላውድ ሥርዓቶችን፣ መረጃዎችን እና የሳይበር መሠረተ ልማቶችን ቴክኖሎጂን በመተግበር እና የአጠቃቀም ፖሊሲዎችን እና የመቆጣጠሪያ ስልቶችን አገልግሎት ላይ በማዋል ከሳይበር ጥቃት የምንጠብቅበት ነው።
ክላውድ በሚጠቀሙ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከሚገጥሙት ዋና ዋና የደኅንነት ፈተናዎች አንዱ ተጠቃሚዎች የግል መረጃቸውን በብዛት በኩባንያዎች የክላውድ ማከማቻ (Cloud Storage) ውስጥ ሲያስቀምጡ የመረጃዎቻቸው ደኅንነት እና ግላዊነት አደጋ ላይ መውደቅ ነው።
ይህ አደጋ የተጠቃሚዎች የይለፍ ቃል ደካማ ሲኾን ወይም የሁለት ደረጃ ማረጋገጫን (TFA) ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ጠላፊዎች (Hackers) በቀላሉ አካውንታቸውን ሰብረው በመግባት የግል መረጃቸውን ከተቀመጠበት የክላውድ ቋት እንዲወስዱ ወይም ይዘቶችን እንዲቀይሩ ያደርጋል።
ይህ ከተጠቃሚው በኩል በሚፈጠር የደኅንነት ችግር የሚከሰት ሲኾን በክላውድ ላይ ያለው መረጃ አስፈላጊው ጥንቃቄ እና ጥበቃ ካልተደረገለት ኩባንያዎቹ ራሳቸው በመረጃ አያያዝ ላይ በሚሠሩት ስህተት የተነሳ ወይም በሥርዓቱ ውስጥ ሊኖሩ በሚችሉ ክፍተቶች ምክንያት የመረጃ ማፈትለክ ሊከሰት እና የብዙ ተጠቃሚዎች ሚስጥራዊ መረጃ ለሦሥተኛ ወገን ሊጋለጥ ይችላል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች መረጃቸውን ሦስተኛ ወገን በኾኑ የክላውድ አገልግሎት አቅራቢዎች (Cloud Service Providers) ላይ ሲያከማቹ የክላውድ አገልግሎት ሰጭ ተቋሙ ራሱ በቂ የደኅንነት ስልቶችን መተግበር አለበት።
የአቅራቢው ደኅንነት ጉድለት በቀጥታ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ሊጎዳ ይችላል።
የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች እና የክላውድ አገልግሎት አቅራቢዎች ቀጣይነት ያለው እና የላቀ የደኅንነት ሥርዓት መገንባታቸውን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
ተጠቃሚዎችም የይለፍ ቃሎቻቸውን በማጠንከር እና ባለብዙ ደረጃ የማረጋገጫ ዘዴዎችን (MFA) በመጠቀም የራሳቸውን ደኅንነት ማጥበቅ ይኖርባቸዋል።
ይህ ማለት የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ደኅንነት በተጠቃሚው፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያው እና በክላውድ አገልግሎት ሰጭው ተቋም ጥንቃቄ ጭምር የሚጠበቅ መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleግብረ ገብነት የጎደላቸውን ነጋዴዎችን ማጋለጥ ይገባል።
Next articleየደም ግፊት በሽታ እንዴት ይከሰታል?