ፖሊሳዊ ሥልጠናዎችን ወደ ተግባር በመተርጎም የሀገርን እና የሕዝብን ሰላም ማረጋገጥ ይገባል።

15
ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ያሠለጠናቸውን የመደበኛ እና አድማ መከላከል ፖሊስ ምልምል ሠልጣኞችን አስመርቋል።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ፣ የብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መኮንን መንግሥቴ እና ሌሎችም ወታደራዊ መኮንኖች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ዩኒቨርሲቲ ኾሌጁ የፖሊስ አባላትን በማሠልጠን የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ዜጎች የሰላም ዋስትና እንዲሰማቸው፣ የመንግሥት የልማት እና የዴሞክራሲ ፖሊሲዎች ውጤታማ እንዲኾኑ የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
ብቃት ያለው የፖሊስ ኃይል አሠልጥኖ ወደ ሥራ በማሰማራት በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር የመቀልበስ እና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ሕዝባዊ እና ሀገራዊ ፍቅር ያለው፣ አንድነቱ የተጠናከረ፣ ማንኛውንም ችግር በግንባር ቀደምነት የሚጋፈጥ እና ከራሱ በፊት የሀገሩን ክብር እና ጥቅም የሚያስቀድም የፖሊስ ኃይል መገንባት ለነገ የማይባል መኾኑን አንስተዋል።
በሥልጠና ወቅት ከመደበኛ ሰዓቶች በተጨማሪ እሁድ እና ቅዳሜ፣ ምሽት ጭምር በመጠቀም ሠልጣኞች የተሻለ ዕውቀት እና ክሕሎት እንዲያገኙ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።
የዛሬው ምርቃት ተቋሙ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ባደገበት ማግሥት መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል። የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በአጠቃላይ የአደረጃጀት እና የአሠራር ለውጥ ላይ መኾኑን እና የዛሬ ተመራቂዎችም የዚሁ የለውጥ ትግበራ አንድ አካል በመኾናቸው ሊኮሩ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ተመራቂ ፖሊሶች የወሰዷቸውን ፖሊሳዊ እና ወታደራዊ ሥልጠናዎች ከአዲስ ሰሜት እና አስተሳሰብ ጋር አዋህደው በመተግበር ክልሉ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማገዝ እንደሚገባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
“ፖሊሳዊ ሥልጠናውን ማጠናቀቁ ብቻውን ውጤት አይደለም፤ ተጨባጩ ውጤት የሚለካው የተገኘው ዕውቀት እና ክሕሎት ወደ ተግባር ሲተረጎም እና የክልሉን ሰላም ማስፈን ሲቻል ነው” ብለዋል።
በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ የሚቃጡ የጸጥታ ችግሮች እና ወንጀሎች አስቀድሞ በመከላከል የሕዝብን ሰላም መጠበቅ እና በሰላም ሠርቶ እንዲኖር ማስቻል አለባችሁ ነው ያሉት።
“ከሁሉም በፊት ለፖሊሳዊ ሥነ ምግባር ተገዥ በመኾን እና ፖለቲካዊ ገለልተኝነትን በመጠበቅ ለሕዝብ ሰላም የምታገለግሉ ሁኑ” ብለዋል በመልዕክታቸው።
ሁሉንም እኩል በማስተናገድ ሌብነትን እና ብልሹ አሠራሮችን የሚጠየፉ፣ ወታደራዊ የዕዝ ሰንሰለቶችን በማክበር የክልሉን እና የሀገሪቱን ሕግ የሚያስከብሩ ሙያተኞች እንዲኾኑም አሳስበዋል። ምክትል ኮሚሽነር አበበ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
የብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መኮንን መንግሥቴ የክልል የጸጥታ ተቋማትን መደገፍ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አንዱ ተልዕኮ ነው ብለዋል።
በዚህም መሠረት ምልምል ፖሊሶች በብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ገብተው በዕውቀት እና ክሕሎት ታንጸው እንዲወጡ እና ለዛሬ ምርቃት እንዲበቁ ማገዛቸውን ተናግረዋል።
ለተመራቂ የአድማ መከላከል እና መደበኛ ፖሊስ ምልምል ሠልጣኞች ለምረቃ በመብቃታቸውም እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋቸዋል።
ባንዳ እና ባዳዎች በመደራጀት ሀገራችን ብሔራዊ ሃብቶቿን እንዳትጠቀም የሚያደናቅፍ የጸጥታ ችግር እየፈጠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል። የዛሬ ተመራቂዎች የክልሉን እና የሀገርን ሰላም በቁርጠኝነት በመጠበቅ ለሀገር እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሥልጠናው ለቀጣይ ግዳጅ በቂ የኾነ ዕውቀት እና ክሕሎት የተገኘበት እንደነበርም ገልጸዋል። በቀጣይ የሚኖራቸው ስምሪትም ሀገራቸውን በቁርጠኝነት የሚያገለግሉበት እና ሙያቸውንም በልምድ የሚያዳብሩበት እንዲኾን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለሰላም አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይገባል።
Next articleፖሊሳዊ ሥልጠናዎችን ወደ ተግባር በመተርጎም የሀገርን እና የሕዝብን ሰላም ማረጋገጥ ይገባል።