
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በማብራሪያቸውም በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ሕወሃት ሕገ ወጥ ምርጫ ነው ያካሄደው ይሰርዝ፤ በዚያ ምርጫ የተቋቋመው መንግሥት ይፍረስ፣ ምክር ቤቱ ይበተን፤ ከሁሉም የተውጣጣ መንግሥት ይቋቋም የሚል ስምምነት ነው ብለዋል።
የታጠቀ በመልሶ መቋቋም ይፈታል እንጂ መሳሪያ ይደብቃል አይደለም ስምምነታችን፤ የተፈናቀሉ ወገኖች ይመለሱ የሚል ስምምነት እንዳለም ተናግረዋል። የውጭ ግንኙነት የፌደራል መንግሥትን ይመለከታል፤ ደኅንነትን በተመለከተ ደግሞ መከላከያ ሠራዊትን ይመለከታል ነው ያሉት። ስምምነቱ ይህንም የሚያከብር እንደኾነ ነው የተናገሩት።
የወሰን ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ ምላሽ እንደሚሰጠው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት ብለዋል። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የተፈናቀሉ ወገኖችን አንመልስም ብለው ይዘው መቀመጣቸውንም ገልጸዋል።
የወልቃይት ጉዳይ በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ መቋጨት እንደሚገባም ተናግረዋል። ይህ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ለወልቃይት በጀት እየሰጠ አይደለም፤ ይህ ትክክል አይደለም ነው ያሉት።
በስምምነቱ መሠረት የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚጠበቅበትን ማድረጉንም ገልጸዋል። የወደሙት ልማቶች መልሰው ማቋቋማቸውን፤ የተቋረጠ አገልግሎት መመለሱን አንስተዋል።
ለትግራይ ክልል የመረጡት መሪ እየተሾመ ነው፤ ነገር ግን አንፈልግም ይላሉ፤ ትግራይ ውስጥ ተጨማሪ ውጊያ እንዲፈጠር አንፈልግም፤ ሰላም እንፈልጋለን ነው ያሉት። ሕወሃት ሕግ ማክበር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ያለኝ ምክር ውጊያ ይበቃናል፤ ብትዋጉም አታሸንፉም፤ የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል መጣል አይቻልም ብለዋል። ለትግራይ እናቶች ሰላም ያስፈልጋል፤ በእኛም በኩል ሰላም እንፈልጋለን ነው ያሉት።
ለትግራይ የሚሰጠው በጀት የሚውለው ለታጣቂዎች መኾኑንም ገልጸዋል። ከውጊያ እና ከግጭት ወጥተው ወደ ልማት መዞር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል። ምክክር ይበጃል ያሉ ተወያይተዋል ነው ያሉት። የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው ጥሩ ሂደት እንደኾነም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
