
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በማብራሪያቸውም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተሠራ ነው፤ በዚህ ዓመት እንደ ሀገር 100 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመድረስ ይሠራል ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡ በብዙ መልኩ እየተቀየረ መኾኑን ተናግረዋል። 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በኮደርስ ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ዲጂታል ኢትዮጵያን የመገንባት ሥራው በጥሩ ሂደት ላይ መኾኑንም አንስተዋል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚያስደንቅ ለውጥ እያመጣ መኾኑንም ገልጸዋል። ለውጦች ኢትዮጵያ ውስጥ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ትምህርት ላይ ታች ድረስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ለመምህራን ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል። 43 ሚሊዮን የማስተማሪያ መጻሕፍት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሠራጨታቸውንም አመላክተዋል።
ትምህርት ለትውልድ በሚለው ንቅናቄ አስደናቂ ውጤት እየመጣ ነው ብለዋል። የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። “ልጆቻችን ላይ ጥንቃቄ ካላደረግን የምንመኛትን ኢትዮጵያ አናያትም”፤ እነርሱን ታሳቢ ያደረገ ሥራ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ ብዙ ሥራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። 63 ሚሊዮን ዜጎች በጤና መድኅን መታቀፋቸውንም ገልጸዋል። የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
