
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በማብራሪያቸውም ለኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋታል ብለዋል። የቆዬው የእርስ በእርስ መጋጨት ማብቃት አለበት ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ ሀገራት በጦርነት ሊያሸንፉ እንደማይችሉ ያውቁታል፤ ባዳዎቹ በደንብ ያውቁታል፤ ተላላኪዎቹ ግን ጉጉት አላቸው ብለዋል። ይህ እሳቤ ኢትዮጵያን ካለመረዳት የመጣ ነው ብለዋል።
በመሳሪያ የሚመጡ ሰዎች ከመሳሪያ ያለፈ ነገር ማሰብ አይችሉም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ብቻ ነው የሚያስፈልገው፣ በሰላም ለመሄድ ደግሞ ትዕግሥት እና ጊዜ ያስፈልጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ችግር አለብኝ ከሚል ኃይል ጋር ለመወያየት ዝግጁ ነው፤ ተወያይተን የተመለሱም አሉ ነው ያሉት።
በሀገር ፍላጎት ከተግባባን እንስማማለን፤ ሸለቆ ለሸለቆ የሚሄዱት ዓላማ የላቸውም፤ ተላላኪዎች ናቸው፤ ታገልንልህ የሚሉትን ሕዝብ እየገደሉ፤ ልማት እያደናቀፉ ታገልን ማለት ምን ማለት ነው? ብለዋል።
የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ ሀገራዊ ምክክር ይደረግ ብለን እየሠራን ነው፤ ሀገራዊ ምክክር ነባር ችግር ይፈታል፤ በደል አለብን ለሚሉ ደግሞ የሽግግር ፍትሕ ለማረጋገጥ እየሠራን ነው ብለዋል።
እወያያለሁ ለሚሉ ሁሉ በሩ ክፍት መኾኑንም ገልጸዋል።
አሁንም ለሰላማዊ ትግል በራችን ክፍት ነው፣ ካልተባበርን እና አንድ ካልኾን በስተቀር የኢትዮጵያን ችግር ልንፈታ አንችልም ነው ያሉት።
ስንተባበር ውስብስብ ችግሮች ይፈታሉ፤ ብንተባበር ለኢትዮጵያ ይበጃል፤ ለሰላማዊ ትግል የተገደበ ነገር የለም ብለዋል። ፓርቲ የሌለበት፣ ምርጫ የሌለበት፣ ሕገ መንግሥት የሌለበት፣ ወጣት የሌለበት እና ተስፋ የሌለበት ሀገር ጋር የተለጠፈ ሁሉ ለኢትዮጵያ ተስፋ ሊያመጣ አይችልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ሲያምርባት ዓይኑ የሚቀላ፣ ሕዳሴ ሲያልቅ ምን ያደርጋል ሕዳሴ ከሰው ያጣላናል የሚል፣ የባሕር በር ጥያቄ ሲነሳ የሚያፍር፣ ለኢትዮጵያ ጥቅም ከጎኗ መቆም የማይፈልግ ራሱን እንደ ማንጎ የሚቆጥር ግራዋ ነው ብለዋል።
ሰላም ያስፈልጋል፣ እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው ብለዋል በሰጡት ማብራሪያ።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
