
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ማብራሪያ መስጠታቸውን ቀጥለዋል። በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ መንግሥት ፕሮጄክት ጀምሮ የመጨረስ ችግር እንደሌለበት ተናግረዋል። ነገር ግን ካለው የፕሮጄክት ፍላጎት እና ስፋት አንጻር በሁሉም ቦታ መድረስ አልቻልንም ነው ያሉት። አሁን ላይ በኢትዮጵያ 346 የመንገድ ፕሮጄክቶች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ወጪ የሚያስወጡ መንገዶች እየተሠሩ ነው ብለዋል። በሥራዎቹ ውስጥ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉም ተናግረዋል። ታላላቅ የመብራት ፕሮጄክቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። በፌዴራል መንግሥት ብቻ የሚገነቡ ታላላቅ ግድቦች መኖራቸውንም አንስተዋል። ሥራው ሰፊ በመኾኑ በትብብር እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። በእኛ ልክ ፕሮጄክቶችን ጀምሮ የሚጨርስ አልነበረም ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ያሉብንን ክፍተቶች እየሞላን፣ ጥንካሬዎችን እያስቀጠልን እንሄዳለን ነው ያሉት። ተረጅነት የመፍጠር አቅምን፣ የሚሠራ ጉልበትን የሚበላ ካንሰር ነው፤ ሰው መሥራት እየቻለ እጁን ለልመና የሚዘረጋ ከኾነ በሽታ ነው ብለዋል። ፕሮጄክቶችን ለመሥራት ሰላም ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ሰላም ብቻ ፕሮጄክት አይሠራም፤ ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ከተረጅነት ለመውጣት እየተሠራ ነው፤ ልመና ብዙ ጣጣ የሚያመጣ ነው፤ ተረጅ ሁልጊዜም የተናቀ ነው፤ “ለክብራችን ስንል ተረጅነትን ማስቆም አለብን”፤ ተረጅነትን ለማስቆም ሥንሠራ ፖለቲካ የሚያደርጉ አሉ ይህ ፖለቲካ አይደለም የክብር ጉዳይ ነው ብለዋል። የተፈናቃዮች ቁጥር እየቀነሰ ነው፤ የቀሩትንም ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው ነው ያሉት። ከተረጅነት ለመውጣት መጨከን ይገባናል ብለዋል። ከጨከን ደግሞ እንችላለን ነው ያሉት። ኢትዮጵያ አሁን ዘመን መጥቶላታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ጊዜ የኢትዮጵያ ጊዜ ነው ብለዋል። ሰፋፊ ውጤት እየታየበት መኾኑን ተናግረዋል። ሕልማችን የኢትዮጵያን ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው፤ ከሕልማችን አንወጣም፤ ሕልማችንን አናሰርቅም ነው ያሉት። በ2032 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቢያንስ ከአፍሪካ ሁለተኛው ይኾናል፤ በ2036 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአፍሪካ የመጀመሪያው ይኾናል፤ ይሄን እናሳካለን፤ ማንም ሊያስቆመን አይችልም ብለዋል። ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ! 👇👇👇 https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
