“በቢሾፍቱ የሚገነባው ኤርፖርት ኢትዮጵያ አፍሪካን ከመላው ዓለም ጋር የምታገናኝበት ይኾናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

8
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በማብራሪያቸውም በቢሾፍቱ የሚገነባው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፕሮጄክት ዲዛይን ማለቁን ገልጸዋል። ፕሮጄክቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ “በአፍሪካ ትልቁ ኤርፖርት የሚኾን እና ኢትዮጵያ አፍሪካን ከመላው ዓለም ጋር የምታገናኝበት ይኾናል ነው” ያሉት። አዲሱ ኤርፖርት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የዜጎችን የቤት ባለቤትነት ችግር መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን የቤት ባለቤት ማድረግ አይቻልም፤ ነገር ግን ቢያንስ በአቅማቸው የሚከራዩበትን መንገድ መፍጠር አለብን ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የሲሚንቶ፣ የብረት፣ የመስታወት እና ሌሎች ፋብሪካዎች እየተሠሩ ነው፤ እነዚህ ደግሞ ለቤት ግንባታ አገልግሎት አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።
የቢሾፍቱ ኤርፖርት እና የቤት ግንባታ በኢትዮጵያ ጨዋታ ቀያሪ ልማቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል። ታላላቅ ፕሮጄክቶችን በትብብር ማጠናቀቅ ከቻልን የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ይወስናሉ ነው ያሉት።
ቆመው የነበሩ ፕሮጄክቶችን በማስጀመር ለውጤት የማብቃት ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። የኮሪደር ልማት የቀደሙ ልምዶችን የሚቀይር፣ አዲስ የኑሮ ዘይቤ እያመጣ ነው ብለዋል። ኮሪደር ብዙ አቅሞች እንዲወጡ እያስቻለ መኾኑንም ተናግረዋል።
የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በስፋት እየተገነቡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
የኮሪደር ልማት ከተሞችን ለነዋሪዎች እና ለጎብኝዎች ምቾት እየፈጠረ እንደኾነ ተናግረዋል። ሃብቶቻችንን በሚገባ መረዳት እና መጠቀም ይገባናል ነው ያሉት።
የቆዩ ታሪኮቻችንን ማወቅ እና መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበኢትዮጵያ የተጀመረው የጋዝ ፕሮጀክት ከውጭ የሚገባ ምርትን በመተካት ከፍተኛ ሃብትን ማዳን የሚያስችል ነው።
Next article“ለክብራችን ስንል ተረጅነትን ማስቆም አለብን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)