ለረጅም ጊዜ የቆዩ ፕሮጄክቶች እንዲጠናቀቁ ምን እየተሠራ ነው?

1
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።
የምክር ቤት አባላትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እና አስተያየት አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ለችግር የማትበገር፣ በአሸናፊነት የምትወጣ ሀገር ናት ብለዋል የምክር ቤት አባላቱ። ኢትዮጵያ አሁን ላይ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግራለች።
ከፖለቲካ ብዥታ ወጥታ አሁን ላይ የጠራ መንገድ ይዛ በመቀጠሏ አቅሟ እየተገለጠ፣ ቶሎ የማደግ ተስፋችን እየለመለመ እና ተጨባጭ እየኾነ መጥቷል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሀገር ጥቅምን አስቀድመን ስንሠራ ምንም የሚሳነን እንደሌለ ሕዳሴ ማሳያ ነው ብለዋል። ከሕዳሴ ግድብ ምርቃት ማግስት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ታላላቅ የልማት ሥራዎችን የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን የሚያሳዩ መኾናቸውንም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ እየታዬ ያለው የልማት ውጤት የሚታይ እና የሚጨበጥ መኾኑንም ገልጸዋል። ነገር ግን ልማቶችን ያላዩ በጥላቻ እና በቅናት የተያዙ ኃይሎች አሉ ነው ያሉት። በቅናት እና በጥላቻ ያሉ ኃይሎች ከጥፋት መንገዳቸው መመለስ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
በሀሰተኛ ወሬኞች የኢትዮጵያ ጉዞ እንደማይገታ ነው የተናገሩት። ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚፍጨረጨሩ ኃይሎች የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ አያስቆምም ብለዋል። መንግሥት ለግብርና ምርት እና ምርታማነት የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መኾኑንም ገልጸዋል።
ነገር ግን በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ አካባቢዎች ለምርት እና ምርታማነት እንቅፋት ኾነዋል፤ ይህን ለማሻሻል ምን እየተሠራ እንደኾነ ጠይቀዋል። ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር እየተሠራ ያለው ሥራ ምን እንደሚመስልም ጠይቀዋል።
በጤናው ዘርፍ የሚስታዋለውን የመድኃኒት አቅርቦት እና የሥርጭት ውስንነት ለመፍታት ምን እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል። የመሠረተ ልማቶችን ለማሻሻል መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የመንገድ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ለረጅም ጊዜ የቆዩ ፕሮጄክቶች እንዲጠናቀቁ ምን እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በዓባይ እና በቀይ ባሕር የተፈጠረች ናት፤ እድገቷም ኾነ ፈተናዎቿ የተመሠረተው በእነዚህ ውኃዎች ላይ ነው። የውኃ ሃብቶቿን ለመጠቀም እያደረገችው ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኢትዮጵያ የባሕር በር የሚያስፈልጋት ለቅንጦት ሳይኾን ከፍታን ለማረጋገጥ ነው።
Next articleበአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት 48 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል።