
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ሁሉም ሀገር የተፈጥሮ ጸጋውን በሌላ ላይ ጉዳት ሳያመጣ የመጠቀም መብት አለው ብለዋል። ሁሉም ሀገር የራሱ ብሔራዊ ጥቅም አለው፤ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋትም አለው ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ኢ ፍትሐዊ እና ኢ ርትዓዊ የበደል መጨረሻው በደል የተፈጸመባት ሀገር ናት ብለዋል። ኢ ፍትሐዊ ውሳኔ ባለበት ሁኔታ የተሟላ ሰላም ሊፈጠር እንደማይችል ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በዓባይ ተጠቀመች እንጅ ማንንም አልጎዳችም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ አሁንም ያላት ግልጽ አቋም ነው፤ የሚሻለን ሀብትን በፍትሐዊነት መጠቀም ነው ብለዋል።
ማንም ሰው በጉልበት ፍላጎቱን ማሳካት አይችልም፤ ይህ የኢትዮጵያ ስሪት አይደለም ነው ያሉት።
የባሕር በር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልካምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነው ብለን እናምናለን፤ የባሕር በር ለማግኘት ውይይት ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ የወሰደውን ጊዜ ያክል ለማግኘት አይወስድባትም ብለዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት መንገድ ሕጋዊ እንዳልኾነም አንስተዋል።
“የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ግልጽ ነው፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል፤ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በርን ለማግኘት ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፤ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችንም ጠይቃለች ነው ያሉት። ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ተባብሮ መሥራት ፍላጎታችን ነው” ብለዋል።
የባሕር በር ጉዳይ የማይቀር ስለኾነ ሀገራት እንዲያሸማግሉን ጠይቀናል፤ ሰላም ያስፈልጋል አወ እንሸመግላን እያሉ ማዘናጋት ከኾነ ግን ብዙ የሚሄድ አይመስለኝም፤ በአንድ ቀንም አንመልሰውም፤ በአንድ ቀንም አላጣናውም ነው ያሉት።
የባሕር በር ጉዳይ የጠየቅነው የውስጥ ጉዳይን ለመሸፋፈን ሳይኾን እውነተኛ ጥያቄ ስለኾነ ነው ብለዋል።
“ማንም ፈለገም አልፈለግም ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም፤ ኢትዮጵያ ታላቅ ናት፤ ኢትዮጵያ ካደገች ብለው የሚሰጉ አሉ፤ ኢትዮጵያ ካደገች ትረዳለች እንጅ ማንንም አትጎዳም” ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላም የመኖር ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል። “ለኤርትራ መንግሥት ያለን መልዕክት ጥይት አስተላላፊ አትሁኑ፤ ሀገር ሁኑ፤ ወደ ጎረቤት ሀገር ጥይት ማስተላለፍ ጥሩ አይደለም፤ ጥይት ማመላለስ ይቅርባችሁ፤ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ ሕገ ወጥ ንግድ፣ ሀሰተኛ ብር አስቀሩ፣ እንደ ጎረቤት ብንተሳሰብ፤ በሰላም ከቀጠላችሁ በሰላም አብረን ለማደግ ፍላጎት አለን የሚል ነው” ብለዋል።
ወደ ውጊያ የመግባት ፍላጎት የለንም፤ ወደ ውጊያ ከገባን ግን አስተማማኝ አቅም ነው ያለን፤ ይህ ግልጽ ነው፤ ወደዚህ እንዳይሄድ መሥራት ይገባናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
