“ሀገራዊ ምርጫው ወቅቱን ጠብቆ ይካሄዳል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

16
ባሕር ዳር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ 7ኛው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ እንደሚካሄድ አሳውቀዋል።
አንዳንዶች የጸጥታ ችግር አለ ብለው እንደሚሰጉ ጠቅሰው መንግሥት ግን ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል በቂ አቅም እና ዝግጅት እንዳለው ተናግረዋል።
ሃሳብ አለኝ ብሎ በምርጫው ለመሳተፍ የሚፈልግ እንደሚሳተፍ እና ፓርላማውም ብዙ ድምጾች የሚሰሙበት እንደሚኾን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
እንደ መንግሥትም እንደ ፓርቲም አማራጭ ድምጾች የሌሉበት ምክር ቤት አይጠቅምም ነው ያሉት።
ምርጫ አልተካሄደም እና የሽግግር መንግሥት ይመስረት ለሚሉ ድምጾችም ምክንያት እንደማይኾን ነው የገለጹት። በዚሁም ፓርቲዎች ተዘጋጅተው መወዳደር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አባላትም ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን ብቻ ሳይኾን ልዩ ልዩ ድምጾች እንዲሰሙ በኀላፊነት እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት። ሁሉም ነገር በመደመር እንጂ ጠቅልሎ የመውሰድ ፍላጎት የለም ብለዋል።
በዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ለሰላም መረጋገጥ ብቃት እና ቁርጠኝነት ያለው የጸጥታ ኃይል ያስፈልጋል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየተሰጣቸውን ኀላፊነት በመወጣት ለሀገር ሰላም እና ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ።