የላቦራቶሪ አገልግሎትን በሀገርም ኾነ በክልል ደረጃ የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ነው።

2

ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አራተኛውን ክልላዊ የሕክምና ላቦራቶሪ ፌስቲቫል እያካሄደ ነው።

ፌስቲቫሉ “ጠንካራ የላቦራቶሪ ሥርዓት ጥራት ላለው የጤና አገልግሎት” በሚል መሪ መልዕክት ነው በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ለአንድ ሀገር የሕክምና አገልግሎት ሥርዓት ውጤታማነት ከሚጠቀሱ ተግባራት መካከል አንዱ ጥራት ያለው የሕክምና ላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት መስጠት ነው ብለዋል።

ፌስቲቫሉ በክልሉ የጤናው ሴክተር እና የሕክምና ላቦራቶሪ ባለሙያዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ያስገኟቸውን ስኬቶች ብቻ ለማክበር ሳይኾን የላብራቶሪው ዘርፍ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ያሳየውን እና እያሳየ ያለውን ለውጥ በሚመጥን ኹኔታ በሁሉም ደረጃ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ነው ብለዋል።

ስለኾነም በሁሉም የጤና ላቦራቶሪዎች አጠቃላይ የአቅም ግንባታ ጉዳይ እጅግ አንገብጋቢ በመኾኑ በተከታታይነት እና በዘላቂነት ላይ የተመሠረተ ኢንቨስትመንት እና ኢኖቬሽንን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክተር ዳንኤል መለሰ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የክልል ኢንስቲትዩቶች ግንባር ቀደም ኢንስቲትዩት እንደኾነ ገልጸዋል።

በዓለም ላይ በኅብረተሰብ ጤና ላይ የሚከሰቱ የጤና ሁኔታዎችን መፍትሄ ለመስጠት የላቦራቶሪ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

በዚህም ምክንያት የላቦራቶሪ ግብዓቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ይህንን ታሳቢ በማድረግ እንደ ሀገርም ኾነ በክልል ደረጃ የማደራጀት ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።

የሕክምና ላቦራቶሪ አገልግሎቶች ለሁሉም የጤና ሥርዓቶች አስፈላጊ እና መሠረታዊ እንደኾኑም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

በበሽታ ምልክቶች ላይ ብቻ ተመርኩዞ የሕክምና አገልግሎት መስጠት የታካሚዎችን ሕመም እና ሞት ከመ ጨመረ ባለፈ ለኅብረተሰቡ የጤና ስጋት እየኾነ የመጣውን የመድኃኒት ብግርነት እንዲሰፋ እያደረገ እንደኾነም ጠቁመዋል።

በፌስቲቫሉ በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት የሕክምና ላቦራቶሪ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ይገመገማሉ፤ እየገጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያም በመወያየት የመፍትሄ ሃሳብ ይቀመጣል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

በዕለቱ በዘርፉ የተሻለ ሥራ ለሠሩ አካላት እና ድርጅቶች ዕውቅና እንደሚሰጥም ታውቋል።

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪ ምገባ ተደራሽነቱ እንዲሰፉ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ይፈልጋል።
Next article“እውቅና እና ሽልማቱ ለሁሉም የፖሊስ ሠራዊት የማንቂያ ደወል ነው” ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር)