በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ86 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብት ማዳን ተችሏል።

10
ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2017 ዓ.ም የክረምት ወራት ሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የዕውቅና መርሐ ግብር “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ተካሂዷል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እንዳሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመንፈስ እርካታ ለማግኘት ሰዎች በፈቃደኝነት የሚሰጡት አገልግሎት ነው። የሰዎችን ሰብዓዊነት የሚያጎለብት አገልግሎት መኾኑንም ገልጸዋል።
በበጎ ፈቃት አገልግሎት ማኅበራዊ መስተጋብር እየጠነከረ መኾኑንም ገልጸዋል። የልማት ክፍተቶችን በመሙላት እና የማኅበረሰቡን መልካም እሴት በማጠናከር ሚናው እየጎላ መምጣቱን ገልጸዋል። ሥራው የአቅመ ደካሞችን ችግር የፈታ መኾኑንም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ከ656 ሺህ በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን ገልጸዋል። ከ13 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግም ተችሏል። በዚህም ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥትን ወጭ መታደግ መቻሉን አብራርተዋል።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) እንዳሉት የበጎ ፈቃድ ሥራ የወጣቶች እና ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው።
በተለይም ደግሞ በመንግሥት እና በማኅበረሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የማይተካ ሚና አለው።
የወጣቶች የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲጠናከር እና የማኅበረሰቡን ጠቃሚ እሴቶች እንዲቀስሙ አድርጓል ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው እና ባሕል ኾኖ እንዲቀጥል የአሠራር ማዕቀፍ በመቅረጽ እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በ14 አይነት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት። ከ35 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችም በሥራው ላይ ተሳትፈዋል።
በዚህም 53 ሚሊዮን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት። ከ86 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብትን ማዳን መቻሉን ነው የተናገሩት።
በ2018 በጀት ዓመትም በበጋው ወራት ጭምር የበጎ ፈቃድ ሥራውን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሳይበር ጥቃት ሉዓላዊነትን እስከ ማስደፈር የሚያደርስ ነው።
Next articleበትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪ ምገባ ተደራሽነቱ እንዲሰፉ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ይፈልጋል።