
ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለፖሊስ አባላቱ የዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
“በጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብዓዊነት ማገልገል” የሥራ ስምሪት መርሁ ነው፤ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ።
ክልሉ ባለፉት ዓመታት ከገጠሙት የሰላም እጦት ቀውሶች ወጥቶ አንጻራዊ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ፖሊስ እስከ ሕይዎት መስዋዕትነት የደረሰ ውድ ዋጋ ከፍሏል።
ከተሞች ካጋጠማቸው የሥርዓት አልበኝነት አደጋ አገግመው መደበኛ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቀጥሉ ፖሊስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል።
በክልሉ የሚዘወተሩ ሕዝባዊ፣ ሃይማኖታዊ እና መንግሥታዊ በዓላት እና ሁነቶች ያለአንዳች እንከን እንዲከበሩ ፖሊስ ቀን ሀሩሩን፣ ሌሊት ቁሩን በጽናት አሳልፏል።
ትናንት ስላሳለፈው ሁሉ ለማመሥገን፤ ቀሪ የቤት ሥራዎቹን በጀግንነት ለመፈፀም ይቻለው ዘንድ በለውጥ ሂደት ላይ ያለው ዋና ጠቅላይ መምሪያው የፖሊስ አባላቱን እያመሠገነ ነው።
የዕውቅና እና የሽልማት መርሐ ግብሩ የትናንቱን በመዘከር ማመሥገን፤ ለመጻዒ ተልዕኮ እና ግዳጅ በሥነ ልቦና ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ ነው።
በዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብሩ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ዓለምአንተ አግደውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
