
ባሕር ዳር:ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በኦሞ ወንዝ ታችኛው ተፋሰስ ከጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ 129 ኪሎ ሜትር ርቀት ከኮይሻ መንደር በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።
1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የኮይሻ የኃይል ማመንጫ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የኃይል ፍሰት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ነው። ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ በዓመት 6 ሺህ 344 ጊጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። ከኃይል አቅርቦት ማስፋፊያነቱ ባሻገር የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ንፁሕ፣ አስተማማኝ እና የተጠቃሚዎችን አቅምን ከግምት ያስገባ ታዳሽ ኃይል አቅርቦት የሚያቀርብ ኢትዮጵያም በምሥራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ የውጭ ንግድ ማዕከል ለመኾን ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሳካት የሚደግፍ ነው።
በሀገር ውስጥም የገጠር ኤሌክትሪክ አቅርቦትን በሚደግፍ መንገድ በመኖሪያ ቤቶች እና በአነስተኛ የንግድ ሥራዎች የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ያሳድጋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ይኽም ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማትን የሚያነቃቃ፣ የተሻሻለ የአኗኗር ደረጃን የሚፈጥር እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዘላቂ እድገትን የሚደግፍ እንደሚኾን ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
