
ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማሥተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።
በዕለቱ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማሥተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ “የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የፖለቲካ ሥርዓታችን ማዘመን ይገባናል” ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በፉክክር እና በትብብር መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ፉክክሩ ጤናማ እና ውጤታማ እንዲኾን የፖለቲካ ምህዳሩን ጤናማ እና ውጤታማ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሕዳሩን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ሕጎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩን ውጤታማ እና ጤናማ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፉን በተገቢው የሚተገብሩ ተቋማት ያስፈልጋሉ ነው ያሉት። የምርጫ ቦርድ ነጻ እና ገለልተኛ ኾኖ መቋቋሙንም ገልጸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም የፖለቲካ ምሕዳሩን ውጤታማ ለማድረግ መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የሀገርን ነባራዊ ሁኔታ የተመቸ ማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ውጤታማ ያደርገዋል ነው ያሉት። የሀገርን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባም አንስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን የሚገልጹበትን መንገድ ማመቻቸት ለፖለቲካ ምሕዳሩ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚመክሩበትን ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል። የጋራ ምክር ቤቱ በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየመከረ መኾኑንም ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግን እና መርሕን ማክበር ይገባቸዋል ያሉት አቶ አደም መርሕን እና ሕግን የማያካበር የፖለቲካ ፓርቲ ባለበት ጤናማ የፖለቲካ ምሕዳር እና ፉክክር ሊኖር አይችልም ነው ያሉት። በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ መታገል እንደሚገባም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሥፈጸም የሚሠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች አሉ ያሉት አቶ አደም ፋራህ እነዚህ ኃይሎች የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በሰላም እንዲያቀርቡ ሚናችን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።
የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሥፈጸም የሚጥሩ ኃይሎች በጋራ ካልታገልን የፖለቲካ ምሕዳሩ ብቻ ሳይኾን የሀገር ሕልውናም አደጋ ላይ ይወድቃል ነው ያሊት።
የጋራ ትብብርን ለማጠናከር በብሔራዊ ጥቅም፣ በዜጎች ሰላም፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር መግባባት ይገባል ብለዋል። እነዚህ ጉዳዮች ላይ ካልተግባባን ትብብሩ ውጤታማ አይኾንም ነው ያሉት።
በጋራ በተግባባነው ላይ በጋራ መሥራት ይገባናል ብለዋል። ይህን ስናደርግ በፉክክር እና በትብብር ላይ ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ ያስችላል ነው ያሉት።
በዛሬው ምክክር የጋራ መግባባት ላይ መፍጠር እንደሚገባም አንስተዋል። በጋራ መግባባት ላይ ፈጥረን የየድርሻችን ይዘን መሄድ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
