
ወልድያ: ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 118ኛው የመከላከያ ሠራዊት የምሥረታ ቀን በዓል በወልድያ ከተማ ከሠራዊቱ እና በከተማዋ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የፓናል ውይይት በማካሄድ ተከብሯል።
የፓናሉ ተሳታፊ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሠራዊቱ ለኢትዮጵያ ልዕልና እየከፈለው ያለውን መስዋዕትነት እውቅና ሰጥተዋል። “ሕዝቡም የሠራዊቱ ደጀን ኾኖ በየግዳጁ ከጎኑ ኾኖ ይቀጥላል” ብለዋል።
የ11ኛ ዕዝ የሠራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ኀላፊ ኮሎኔል አክሊሉ አበበ የመከላከያ ሠራዊት ተቀዳሚ ምርጫ እና ዓላማ ሰላም መኾኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ግጭት ወንድም ከወንድሙ ጋር የሚካሄድ በመኾኑ ሞት እንዲቆም ኢትዮጵያውያን በጋራ ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
“የሕዝብ ሰላም ያስጨንቀናል፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሲደፈር ያበሳጨናል” ያሉት ኮሎኔል አክሊሉ አበበ ሠራዊቱ ለኢትዮጵያ ሲል መስዋዕትነት እየከፈለም ቢኾን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና የኢትዮጵያን ህልውና የማጽናት ተግባሩን በዘላቂነት ይቀጥላል ብለዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኢቶጲስ አያሌው አባቶቻችን በኢትዮጵያዊነት ገመድ ተሳስረው ነጻነቷን የጠበቀች ሀገር አስረክበውናል ብለዋል።
የዚህ ዘመን ትውልድም የሠራዊቱ ደጀን በመኾን የኮራች ሀገር ለመጪው ትውልድ የማሻገር ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው፤ ለዚህም በሰሜኑ ጦርነት የወልድያ ከተማ ሕዝብ ያሳየው ተጋድሎ ምስክር ነው ብለዋል። ይህ ደጀንነት ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
